ህወሃት የኤርትራ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ወዳሉባቸው አካባቢዎች መግባቱን ተከትሎ እስካሁን ድረስ ቢያንስ ስድስት ስደተኞች ተገድለዋል – ኤጀንሲው

ሐምሌ 15/2013 (ዋልታ) – ህወሃት የኤርትራ ስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ወዳሉባቸው አካባቢዎች መግባቱን ተከትሎ እስካሁን ድረስ ቢያንስ ስድስት ስደተኞች እንደተገደሉ በኢፌዴሪ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ አስታውቋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞችን አስመልክቶ በኢፌዴሪ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ የተሰጠውን መግለጫ ሙሉ ቃል እነደሚከተለው ቀርቧል፦

በማይ-ዓይኒ እና አዲ-ሐሩሽ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ያሉበትን ሁኔታ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲረዳና አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ በቅርቡ በሰጠነው መግለጫ ጥሪ ማቅረባችን ይታወቃል።

ያጋጠሙ ችግሮችን ለማስወገድ በተደረገው ጥረት በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ እየተቋቋመ ያለውን መጠለያ ጣቢያ ለማፋጠን ጠንክረን እየሰራን ሲሆን ከግጭቱ ቀጠና ለወጡ ስደተኞች የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን እና አገልግሎቶችን በማደራጀት ላይ እንገኛለን።

ይህንን ለማሳካትም ትምህርት ቤቶችን በጊዜያዊ መጠለያነት ለመጠቀም እንድንችል ከአከባቢው የመንግሥት ኃላፊዎች ፈቃድ እና ሙሉ ድጋፍ አግኝተናል።

አስፈላጊ የእርዳታ ቁሳቁሶች ወደ አካባቢው የተጓጓዙ ሲሆን ጥቂት አጋሮችም ምላሽ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

ስለሆነም ስደተኞችን መቀበል፣ በጊዜያዊነት በትምህርት ቤቶች ማስጠለል እና ትኩስ ምግብ ማቅረብ ጀምረናል።

ሆኖም ስደተኞቹ ያሉበት ሁኔታ አስከፊ ወደ ሆነ ደረጃ እየተሸጋገረ በመሄዱ እጅግ አሳሳቢ ሆኗል።

ህወሃት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ወዳሉባቸው አካባቢዎች መግባቱን ተከትሎ እስካሁን ድረስ ቢያንስ ስድስት ስደተኞች እንደተገደሉ የሚያሳዩ መረጃዎች ተገኝተዋል።

ዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብት ሕግ በመጣስ የህወሃት ታጣቂዎች በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ከባድ መሣሪያዎችን የተከሉ ሲሆን ቀጣይነት ያለው የታጣቂ እንቅስቃሴ እና አልፎ አልፎም የተኩስ እሩምታ በማሰማት ላይ ይገኛሉ።

በተጨማሪም ለሰብአዊ አገልግሎት እንዲውሉ የተዘጋጁና የተቋቋሙ ጤና ጣቢያዎችን ጨምሮ አምቡላንሶችን እና መሰረተ ልማቶችን ለወታደራዊ አገልግሎት እያዋሉ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በዚህም ምክንያት ቢያንስ ሁለት ስደተኞች በጤና አገልግሎት እጥረት መሞታቸው የተገለጸ ሲሆን እናቶች አስጊ በሆነ ሁኔታ እየወለዱ ይገኛሉ።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም መጋዘኖችን ጨምሮ የኤጀንሲያችን እና የሌሎች አጋሮች ንብረቶች እንደተዘረፉ መረጃዎች ደርሰውናል።

ስደተኞች ለጦርነቱ የሚውል በዓይነትና በገንዘብ መዋጮ እንዲከፍሉ እየተገደዱ ይገኛሉ።

በተጨማሪም ስደተኞቹ ከግጭቱ አካባቢ ለመልቀቅ የሚያደርጉት ጥረት ሁሉ በህወሃት የተከለከለ ሲሆን፣ የሚገኙበት ሁኔታ ከእገታ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ የሚመላክቱ ሁኔታዎች አሉ።

በተቃራኒው ስደተኞችን በጅምላ ወዳልታወቁ ቦታዎች በኃይል የማጓጓዝና እና የተወሰኑትን በህዳር ወር ችግሩ እንደተከሰተ በራሳቸው በህወሃት ታጣቂዎች ጥቃት ደርሶባቸው ወደ ተዘጉት ህጻፅና እና ሽመልባ መጠለያ ጣቢያዎች እንዲዛወሩ የማድረግ ሙከራዎች እንዳሉ መረጃዎች ደርሰውናል።

እስከ ዛሬ ድረስ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ወደ ማይ-ጸምሪ ወደ ሚገኙት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች መግባትም ሆነ ለስደተኞች አገልግሎት መስጠት አልቻሉም።

የኢትዮጵያ መንግስት የስደተኞች ደህንነት ለመጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት በድጋሜ እያረጋገጠ፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተፈፀሙ በጭካኔ የተሞሉ ወንጀሎችን በማያሻማ ሁኔታ እንዲያወግዝ ጥሪውን ያቀርባል።

በተጨማሪም ስደተኞች ከሚገኙበት አደገኛ ሁኔታ እና የእገታ አዝማሚያ ለመታደግ የምናደርገውን ጥረት እንዲደግፍ እና በስደተኞች ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ለማጣራት የምናደርገውን ጥረት እንዲያግዝ ጥሪ እናቀርባለን።