ህወሐት እያደረገ ያለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳሳሰባቸው ሳማንታ ፓወር ገለጹ

ሐምሌ 28/2013 (ዋልታ)- ህወሐት እያደረገ ያለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳሳሰባቸው የአሜሪካው ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤድ) ኃላፊ ሳማንታ ፓወር ገለጹ።

ህወሐት በተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ መሰየሙ ይታወሳል።

በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የአሜሪካው ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤድ) ኃላፊሳማንታ ፓወር በኢትዮጵያ ዛሬ ምሽት ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ቀደም ብለው በትግራይ ክልል ስላለው የሰብዓዊ ድጋፍ በተመለከተ ከሠላም ሚኒስትርና ከሌሎች የሥራ ሃላፊዎች ጋር ገንቢ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ የሚቀርበው የሰብዓዊ ድጋፍ አሁንም መፋጠን እንዳለበት ጠቁመው በዚህም ከመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ጋር መግባበትላይ መድረሳቸውንጠቁመዋል።

ይሁንና በዚህ የሰብዓዊ ቀውስ ወቅት የሕወሃት ወደ አጎራባች ክልሎች የሚያካሂደው ወታደራዊ እንቅስቃሴ አንዳሳሰባቸው ነው ሃላፊዋ የተናገሩት።

በሕወሃት በሚያደርገው ወታደራዊ እንቅስቃሴ በአማራ ክልል150 ሺህ ሰዎች በአፋር ክልል ደግሞ 76 ሺህ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን ነው ያረጋገጡት።

የአሜሪካው ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤድ) ኃላፊ ሳማንታ ፓወር ላለፉት አራት ቀናት በሱዳን ጉብኝት አድርገዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተሰየመው የህወሐት ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ በተግባር በመንቀሳቀስ በሀገር መከላከከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈፀሙን ጨምሮ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ሰብአዊ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ይታወቃል።