ህዝበ ክርስቲያኑ በመረዳዳትና በኢትዮጵያዊ አንድነት በዓሉን ማክበር ይገባዋል – የኃይማኖት አባቶች

የኃይማኖት አባቶች

ህዝበ ክርስቲያኑ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓልን ስያከብር የታመሙትንና የታሰሩትን በመጠየቅ፣ የተራቡትንና የተጠሙትን በማብላትና በማጠጣት እንዲሁም የታረዙን በማልበስ ሊያከብር እንደሚገባ የኃይማኖት አባቶች አሳሰቡ፡፡

የኢየሱሰ ክርቶስ ልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ የኃይማኖች አባቶች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤቴክርስቲያን ብጹዕ ወቅዱስ ቀዳማዊ ፓትሪያሪክ አቡነ ማቲያስ ከጥንት ጀምሮ የነገረንን ተስፋውን ለመፈጸም በዚህ ዓለም የተወለደው የተስፋ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሀገር ውስጥ፣ በውጭ ሀገራት፣ በየማረሚያ ቤቶች ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና በተለያዩ ቦታዎች በዓሉን ለሚያከብሩት እንኳን በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል፡፡

ልደተ ክርስቶስ የተለያዩት የተገናኙነበት፣ የተራራቁት የተቀራረቡበት፣ ሰማያዊያንና ምድራዊያን ስለእግዚአብሔር ክብርና ስለሰላም በኅብረት የዘመሩበት ታላቅ በዓል ነው ያሉት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ ስለእግዚአብሔር ክብርና ስለሰላም አስፈላጊነት ከልደተ ክርቶስ የበለጠ አስተማሪና ትምህርት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ህዝበ ክርስቲያኑ የክርስቶስን ልደት በዓል ስያከብር ለአግዚአብሔር ክብር በመቆም እና ለሰው ልጅ ሰላምን ለመስጠትና ለመቀበል በመዘጋጀት ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የ2013 ዓ.ም የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን በማስመልከት ለመላው ምዕምናን ባስተላለፉት መልዕክት “በአየሱስ ክርስቶስ የልደት ቀን እራሳችንን ለእግዚአብሔር በማቅረብ በልጅነት መንፈስ ተቀድሰን በጽድቅና በሕይወት መንገድ መጓዝ ይገባናል” ብለዋል፡፡ ለዚህም በክርስቶስ ምሕረት በመደገፍ በፍቅር ተሳስረን ልንኖር ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

“መላው ክርስቲያን ምዕመናን ከሁሉ በሚበልጠው የጌታችን የእየሱስ ክርስቶስ ትዕዛዝ “የተቸገርውን መርዳት” በሚለው ቃል መሰረት ለችግረኞችና ለምስኪኞች በተለይ በአሁኑ ጊዜ በስደት፣ በመፈናቀልና በመከራ ላይ የሚገኙ ወገኖች በማገዝ፣ በመደገፍና በጌታ ፍቅር መልካም ነገሮችን በማድረግ በዓሉን በጋራ በማክበር ክርስቲያናዊ ግዴታችሁን እንድትፈፅሙ አደራ ማለት እወዳለሁ” ሲሉም አሳስበዋል፡፡

በሀገሪቱ በየጊዜው የምታየውና የምሰማው የሰው ልጆች ለቅሶና ሰቆቃ እንዲሁም መፈናቀል ክቡር የሆነውና እግዚአብሔር በአርዓያውና በአምሳሉ የፈጠራቸው ሰዎች በከንቱ ሕይወታቸው ልባችንን እያሳዘነ ማለፉ እንዲያበቃ ሁላችንም የሰላም ሰዎች በመሆን በወንድማማችነትና በእህትማማችነት መንፈስ የጎሳ፣ የዘር፣ የቀለም፣ የጾታና የዕድሜ ልዩነት ሳይለያየን እንደ አንድ ቤተሰብ በመሆን ልንተባበር፣ ልንረዳዳና ልንተጋገዝ፤ አንድ ሆነን ልንቆም ይገባናል ሲሉም ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

መንግሥትም የሰዎች የመኖር መብትና የሕግ የበላይነት እንዲከበርና ሰላም እንዲሰፍን የተያያዘውን ጥረት አጠናከሮ እንዲቀጥል የጠየቁት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ፣ ለዚህ ሁላችንም በጌታ ልደት የሰላም ሰዎች በመሆን ወደ እርሱ እንመለስ ተግተንም እንጸልይ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት ፕሬዝዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ በበኩላቸው፣ ለኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ምዕመን እና ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት መታሰቢያ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በርካታ ወገኖች በሰላም እጦት ከቀየአቸው ተፈናቅለው በችግር ውስጥ መኖራቸውን የገለጹት ፓስተር ጻድቁ፣ በተለያዩ ስፍራዎች ሰዎች በማንነታቸው እንደሚገደሉ መከራን እንደሚቀበሉና የሰው ልጅ በገዛ ወገኑ ለህሊናው የሚከብድ ግፍ እንደሚፈጽም ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም ምዕመናን ለምድሪቱ ሰላም ተግቶ መጸለይ፣ የተጎዱትን መደገፍና መርዳት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ክርስቶስ የሰውን ልጆች ችግሮችን ሁሉ እንደተካፈለ እኛም የሌሎችን ሰዎች ችግር ለመካፈል፣ ለህመማቸው መፈወስ ለመስራት እና የደስታቸው ምክንያት እንጂ የሀዘናቸው መንስኤ ላለመሆን የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡

መላው ሕዝቦች የዓለማችንና የአገራችን ስጋት ከሆነው ከኮቪድ-19 በሽታ እራሳቸውን ለመከላከል፣ ተገቢውን የመከላከያ ዘዴዎችን ሳይሰለቹ በመጠቀምና በመተግበር ከበሽታው እራሳቸውን እንዲጠብቁም የኃይማኖት አባቶች ባስተላለፉት መልዕክታቸው አስገንዝበዋል፡፡

በመጨረሻም በወጭ አገር የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮያውያን መልካም ኑሮና ሕይወት እንዲኖራችሁ፣ በህመም ላይ በየሆሰፒታሉና በየቤታችሁ የምትገኙ ፈዉስን፣ በየማረሚያ ቤት የምትገኙ ታራሚዎች መፈታትን፣ በስደት ላይ የምትገኙ ወገኖቻችን ወደ አገራችሁና ወደ ቄያችሁ በሰላም መመለስን፣ የአገርን ድንበርና የሕዝቦችን ሰላም ለማስከበር በየጠረፉ የምትገኙ የመከላከያና የፌደራል ፖሊስ አባላት የሥራ ሰኬትን በመመኘት እንኳን ለ2013 ዓ.ም ለጌታችን ለመደኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

(በአድማሱ አራጋው)