ለሀገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ለሚንቀሳቀሰው የሀረሪ ክልል የፖሊስ አባላት ሽኝት ተደረገ


ሐምሌ 11/2013 (ዋልታ)- ለሀገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ለሚንቀሳቀሰው የሀረሪ ክልል የፖሊስ አባላት የሽኝት መርሃ ግብር ተካሄደ፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ትናንት ምሽት በተካሄደ የሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ እንዳሉት የክልሉ ፖሊስ የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥና የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ እያከናወነ ካለው ተግባር በተጨማሪ ሀገራዊ ጥሪን ተከትሎ በከፍተኛ ተነሳሽነት በግዳጁ ላይ ለመሳተፍ ያሳየው ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው።
በተለይም በአሁኑ ወቅት መደጋገፍ እና አንድነት አስፈላጊ በመሆኑ የአሸባሪው የወያኔ ጁንታ ሀገርን የመበተን ሴራ ለመቀልበስ አንድነትን በማጠናከር መመከት ይገባል ብለዋል።
እድሉን ያገኛቹ አባላት ሀገራችን ችግር ባጋጠማት ወቅት ሀገርን በማዳን ተግባር በመሳተፋችሁ ልትኮሩ ይገባል ብለዋል።
በተልዕኮ የሚሰማራው የክልሉ ፖሊስ በግዳጅ ወቅትም የተሟላ ስብዕና እና ስነምግባር በመላበስ ህዝባዊነቱን እንደሚያረጋግጥ እና ተልእኮውን በብቃትና በሀገር ፍቅር ስሜት እንደሚወጣ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
ቡድኑ ስፍራው በዛሬው ዕለት ተልዕኮውን ወደሚወጣበት ግንባር እንደሚንቀሳቀስም ተመልክቷል።
የፖሊስ አባላቱ በበኩላቸው በሀገር ላይ የተደቀነውን ችግር ለመቅረፍ መሳተፍ በመቻላቸው እንዳስደሰታቸው በመግለፅ በተልዕኮውም በላቀ ተነሳሽነትና የሀገር ፍቅር ስሜት ግዳጃቸውን ለመወጣት እንደተዘጋጁ መናገራቸውን ከሐረሪ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።