ሐምሌ 11/2013 (ዋልታ) – ለሀገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ለሚንቀሳቀሰው የሶማሌ ክልል ልዩ ሀይል ሽኝት ተደረገ፡፡
በሽኝት መርሀ ግብሩ ላይ የሶማሌ ክልል ም/ል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሁመድ፣ የሶማሌ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ሀላፊ ኢንጂነር መሀመድ ሻሌ፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የክልሉ ካቢኔ አባላት ተገኝተዋል።
የሶማሌ ክልል ም/ል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሁመድ በሽኝት መርሀ ግብሩ ላይ ባሰሙት ንግግር “ትናንት ወገናችንን ሲጨፈጭፍ የኖረው አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሀገር ለማፍረስ እየጣረ ባለበት በዚህ ወቅት ሀገር የማዳን ኃላፊነትን ተሸክማችሁ ስትሄዱ የክልሉ መንግስትና ህዝብ ሁሌም ከጎናችሁ መሆኑን አረጋግጥላችኋለሁ” ብለዋል።
ትውልድ የማይዘነጋውን ገድል ለመፈፀምና በታሪክ ማህደር ላይ የራሳችሁን እንዲሁም የክልላችንን ስም ለማስፈር በምታደርጉት ጥረት ልትኮሩ ይገባልም ብለዋል።
ሽኝት የተደረገላቸው የልዩ ሀይል አባላት በበኩላቸው ታሪካዊ በሆነው ሀገራዊ ግዳጅ ላይ ለመሳተፍ በመሄዳቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ም/ል ርዕሰ መስተዳድሩ በግዳጅ ላይም የሀገርና የወገን ደጀን በመሆን ከህዝብ የወጡ የህዝብ አገልጋይ ሰራዊት መሆናቸውን እንደሚያስመሰክሩ መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።