ለህዳሴ ግደብ ከ500ሺህ የአሜሪካን ዶላር በላይ ተሰበሰበ


ሐምሌ11/2013 (ዋልታ) –
በበድር ኢትዮጵያ ዓለም ዓቀፍ የሙስሊሞች ማህበርና ዋሽንግተን በሚገኘው የኢፌዴሪ ኤምባሲ አስተባባሪነት ‘ግድቡ የኔ ነው’ በሚል መሪ ቃል የተጀመሪው ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ሃብት የማሰባሰብ መርሃ ግብር ነው ድጋፋ የተሰበሰበው።
በበይነ መረብ (shorturl.at/wCHVZ) በተካሄደው ድጋፍ የማሰባሰብ ስራ ከአምስት መቶ ሃያ ሺህ የአሜሪካን ዶላር በላይ የተሰባሰበ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ድጋፉ አምስት መቶ አርባ አምስት ሺህ ዶላር ደርሷል።
ይህን ታላቅ ሃገራዊ ዓላማ እያስተባበሩ ላሉ የበድር ኢትዮጵያ አመራሮችና ድጋፍ ላደረጉ ወገኖች በሙሉ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጽየያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ ምስጋና አቅርበዋል።
ሌሎች ማህበራትም ይህን ፈለግ በመከተል በዚህ ታሪካዊ ወቅት ድጋፍ የማሰባሰቡን ዘመቻ እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የበድር ኢትዮጵያ አመራሮችና አባላትም ድጋፉ አንድ ሚሊየን ዶላር ለማድረስ እንደሚሰሩ ገልጸው፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ለዚህ ስኬት ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
እስካሁን በተደረገው የድጋፍ ማሰባሰብ ሂደት ጉልህ አስተዋጽኦ ላደረጉ ግለሰቦች የምስጋና እና የእውቅና ስጦታ መበርከቱን ኢፕድ ዘግቧል።