ለሕወሓት ከ800 ሺሕ ብር በላይ ሊያስተላልፉ የሞከሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ግንቦት 25/2014 (ዋልታ) በሰሜን ወሎ ዞን ላስታ ወረዳ ለአሸባሪው ሕወሓት ከ800 ሺሕ ብር በላይ የሆነ ጥሬ ገንዘብ ሊያደርሱ የነበሩ 11 ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የወረዳው ፖሊስ አስታወቀ።
የወረዳው ፖሊስ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ኮማንደር ተገኘ ወርቁ እንደገለፁት በህገ ወጥ መንገድ ለአሸባሪው ሕወሓት ጥሬ ገንዘብ ለማስተላለፍ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለመግታት ክትትል እየተደረገ ነው።
ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ባደረገው ክትትል ባለፉት ሶስት ቀናት ለአሸባሪው ቡድን ሊተላለፍ የነበረ 804 ሺሕ 260 ብር ከነተጠርጣሪ አዘዋዋሪዎቹ ጋር በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ገልፀዋል።
ከተያዘው ጥሬ ገንዘብ ውስጥ 594 ሺሕ 260 ብር ያህሉ ትናንት ሌሊት በባጃጅና በባለ አንድ ጋቢና ቶዮታ መኪና በኬሻ ተሸፍኖ ሊያልፍ ሲል በፀጥታ ኃይሉ በቁጥጥር ስር መዋሉን ኮማንደር ተገኘ ጠቁመዋል።
በህገ ወጥ መልኩ ለሽብር ቡድኑ ጥሬ ገንዘቡን ለማድስተላለፍ በመሞከር ወንጀል የተጠረጠሩ 11 ግለሰቦችና አንድ ባጃጅ በህግ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑንም ለኢዜአ ተናግረዋል።
የህገ ወጥ ንግድንና የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል ኅብረሰተሰቡ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልና በወረዳው የሌሊት ጉዞ የተከለከለ መሆኑን በመገንዘብ አካባቢያቸውን በንቃት እንዲጠብቁ ኮማንደሩ ጥሪ አቅርበዋል።