ለመከላከያ ሠራዊት ከ53 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ

ጳጉሜ 4/2014 (ዋልታ) ለኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከ53 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ተደረገ።

ከተደረገው ድጋፍ መካከል ከ25 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆነውን ድጋፍ ያደረገው የሲዳማ ክልል ነው።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ድጋፉ አዲሱን ዓመት ከጀግኖቹ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጋር ማክበርን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።

አሸባሪው ቡድን ለሶስተኛ ጊዜ በከፈተው ጦርነት ሀገር ወደዚህ እንድትገባ መገደዷን አንስተው፤ ጀግናው የመከላከያ ሰራዊትና ሌሎችም የጸጥታ አካላት እያስመዘገቡ ባሉት አኩሪ ድል ሀገር ዳር ድንበሯ እየተጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሰራዊቱ አባላት ለህዝቡ ደህንነትና ለሀገር ክብር ለሚያደርጉት ትግል መላው የክልሉ ህዝብ ደጀንነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል፡፡

በዚህም ከ25 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ የሚያወጡ የተለያዩ ድጋፎች ከሁሉም መዋቅሮች መሰባሰቡን አስታውቀዋል፡፡

ከድጋፎቹ መካከል 200 ሰንጋ በሬዎች፣ 400 በግና ፍየሎች፣ ከ1 ሺሕ 100 ሊትር በላይ ዘይት፣ 300 ኩንታል የዳቦ ዱቄትና 40 ኩንታል በሶ ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪም የክልሉ መንግስት በግንባር ያሉ የሰራዊቱ አባላት እንዲገለገሉባቸው 2 አምቡላንሶችንና ህዝቡ የለገሰውን 282 ዩኒት ደም መስጠቱን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡

የትግራይ ህዝብ ቡድኑን በመቃወም የመንግስትን የሰላም ጥሪ እንዲቀበል ማስገደድ እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡

በተመሳሳይ የምዕራብ አርሲ ዞን ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የእርድ ሰንጋና የስንቅ ድጋፍ አድርጓል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አሕመድ ሐጂ በወቅቱ እንደገለፁት ድጋፉ 374 ሰንጋዎች እንዲሁም የተዘጋጀ በሶ፣ ቆሎና ስኳር መሆኑን ጠቁመው፣ ህዝቡ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንድቀጥልም ጠይቀዋል።

የምዕራብ አርሲ ዞን ህዝብ የአሸባሪውን ህወሓት ትንኮሳ ለማምከን በግንባር እየተፋለመ ላለው የመከላከያ ሰራዊት የደጀንነት ሚናውን እስከፍፃሜው ድረስ ይወጣል ሲሉም ተናግረዋል።

ድጋፉ የሰራዊቱንና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎችን የውጊያ ሞራል በመፍጠር ለድል የሚያበቃ ነው ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

ድጋፉ አሸባሪው ህወሓት የመንግስትን የሰላም ጥሪ ወደጎን በመተው ለሶስተኛ ጊዜ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት በግንባር መስዋእነት እየከፈለ ያለው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጠንካራ ደጀን እንዳለው ማሳያ ነው ሲሉም አክለዋል።