ለሠራዊቱ ድጋፍ ለሚሰጡ የኪነጥበብ ባለሙያዎች የሽኝት ሥነ-ሥርዓት እየተካሄደ ነው

ነሀሴ 07/2013 (ዋልታ) – በዘመቻ ሥራዎችና በማሰልጠኛ ተቋማት ለሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በኪነጥበባዊ ሥራዎች ድጋፍ ለሚሰጡ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር  ማዘጋጃ ቤት የሽኝት ሥነ-ሥርዓት እየተካሄደ ነው።

የኪነ ጥበብ ባለሙያዎቹ በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ  ከሚገኙ የትያትር ቤቶች የተውጣጡ ናቸው።

የዚህ መርሀ-ግብር አዘጋጅ የሆነው የአገር ፍቅር ትያትር ቤት ሥራ አስኪያጅ አርቲስት አብዱልከሪም ጀማል ለኢዜአ እንደገለጹት በዛሬው እለት ሽኝት የሚደረግላቸው ባለሙያዎች  በዘመቻ ሥፍራዎችና በማሰልጠኛ ተቋማት ለሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በኪነጥበባዊ ሥራዎች ድጋፍ የሚሰጡ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ናቸው።

ባለሙያዎቹ በሚሄዱባቸው ሥፍራዎች ለመከላከያ ሠራዊቱ መነሳሳትን የሚፈጥሩ የሙዚቃ የትያትርና ሌሎች የኪነጥበብ ሥራዎችን እንደሚያቀርቡ ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ፋይዛ መሐመድ ኪነ ጥበብ የአገርን ህልውና ለማስጠበቅ ለተካሄዱ ዘመቻዎች ከፍተኛ ድጋፍ ሲሰጥ ነበር ብለዋል።

አሁንም በሙያችኹ ለመከላከል ሠራዊቱ የሞራል ስንቅ በመሆንና በሙያችኹ ድጋፍ በመስጠት አገር ለማፍረስ የመጣውን አሸባሪ ቡድን ማስወገድ ይገባል ነው ያሉት።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የከተማዋ የስራ ኃላፊዎችና የኪነጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።