ለሽብርተኛው ህወሓት ሐሰተኛ መረጃ ጆሯችንን ሳንሰጥ የጀመርነውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን – የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች

ነሐሴ 3/2013(ዋልታ) – የሽብርተኛው ህወሓት ቡድን አባላት ለሚያሰራጩት ሐሰተኛ መረጃና አሉባልታ ጆሯችንን ሳንሰጥ የጀመርነውን ድጋፍ አጠናክረን መቀጠል አለብን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ የኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን የሚደግፍ እና አሸባሪውን የህወሃት ቡድን የሚያወግዝ ሰልፍ ተካሂዷል።

የሰልፉ ተሳታፊ አብዲ ገነሞ ከዚህ በፊት ለአገሩ በወታደርነት ደሙን ማፍሰሱን ገልጾ፤ አሁንም በሚችለው አቅም የህልውና ዘመቻውን እንደሚደገፍ ተናግሯል።

የራስን አገር ለመጠበቅ ከውሸት መረጃዎች መቆጠብ እንደሚያስፈልግ አመልክቶ፤ “በመሃከላችን ሆነው የውሸት መረጃ የሚያሰጩ የሽብር ቡድኑ ተባበሪዎችን ልንጠነቀቃቸውንና ልናጋልጣቸው እንዲሁም በሕግ ፊት ልናቀርባቸው ይገባል” በማለትም  አስረድቷል።

ሌላኛዋ የሰልፉ ተሳታፊ ሞትባይኖር ዘበርጋ “እኛ ሴት ኢትዮጵያውያን ሁሉንም ዋጋ በመክፈል አገራችንን ለማስቀጠል እንሰራለን፣ ሆኖም በመካከላችን ሆነው ሃሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ አካላትን ልንጠነቀቃቸው ይገባል” ብላለች።

የተሳሰተ መረጃ በተለያዩ መንገዶች የሚያስተላለፉ የሽብርተኛውን አባላት እንቅስቃሴ በማጋለጥ በአካባቢዋ እየሰራች መሆኑን ገልጻ፤ ሁላችንም ለአሉባልታ መረጃዎች ጆሯችን ሳንሰጥ የጀመርነውን ድጋፍ አጠናክረን መቀጠል አለብን ነው ያለችው።

ቶፊቅ ጀማል በበኩሉ “ይህ ዘመቻ ኢትዮጵያን የመታደግ ዘመቻ ነው፤ የትኛውም የውጭ ሃይል በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚያሳየው ጣልቃ ገብነት አይሳካም፤ እኛም ሉዐላዊነትታችንን አስከብረን ቀጣዩ ትውልድ አሻራችንን እንዲዘክር ማድረግ አለብን” ሲል ነው የገለጸው።

“በኢትዮጵያዊ አንድነታችን ላይ የመጣብንን አካል ባለመደራደር የሚያሰራጨውንም ሀሰተኛ መረጃ ከውጭ እንደመጣ ወራሪ ሃይል በመቁጠር መመከት ይገባል” ነው ያለው።

እንደ ኢዜአ ዘገባ በሃገር ውስጥ የልማት ስራዎችና በዲፕሎማሲውም ዘርፍ ከፍተኛ ስኬት ለማስፈጸም እጅ ለእጅ በመያየዝ ልንሰራ ይገባልም ሲሉ አስተያየት ሰጪዎቹ አመልክተዋል።