ለሽብር ተግባር ሊውል የነበረ 40 ቦምብ ተያዘ

ጥቅምት 4/2015 (ዋልታ) ለሽብር ተግባር ሊውል የነበረ 40 F1 ቦምብ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

በምዕራብ ጎንደር ዞን በመተማ ወረዳ በማጠቢያ ንዑስ ወረዳ ጉባይ ቀበሌ የቅማንት ኮሚቴ ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር በመሆን ለሽብር ተግባር ሊያውሉት የነበረ 40 F1 ቦምብ ከሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር መያዙ ተገለጸ፡፡

ከአማራ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ እንዳመላከተው በህዝብ ጥቆማና በጸጥታ ኃይሉ ክትትል በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የመተማ ወረዳ ፖሊስ የታክቲክ ምርመራ ክፍል ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር ቸኮል ወርቄ ገልጸዋል።

የቅማንት ኮሚቴ ቡድን ከአሸባሪው ህወሓት ጋር በመሆን በተለያዩ ተቋማት እና ሰዎች በብዛት በሚሰበሰቡበት አካባቢ በማፈንዳት በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ አስበው እንደነበር በምርመራ ማረጋገጣቸውን የታክቲክ ምርመራ ክፍል ኃላፊው ተናግረዋል።