ለተፈናቀሉ ወገኖች በጥሬ ገንዘብና በአይነት 20 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተደረገ

ታኅሣሥ 22/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በአማራ ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች በጥሬ ገንዘብና በአይነት 20 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረጉ።

ተቋማቱ ድጋፉን ለአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ዛሬ አስረክበዋል።

ከድጋፉ መካከል በአይነት 13 ሚሊዮን ብር ያበረከተው ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ሲሆን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ደግሞ 4 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የአይነትና በጥሬ ገንዘብ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።

በተቋማቱ የተደረገው አይነት ድጋፍ የህፃናት አልሚ ምግብ፣ የምግብ ዘይትና፣ አልባሳትን ያካተተ ነው።

የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም በርክክብ ስነሥርዓቱ ላይ እንዳሉት የሽብር ቡድኑ ወረራ ፈፅሞባቸው በነበሩ አካባቢዎች በርካታ ዜጎች የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ይፈልጋሉ።

በሽብር ቡድኑ ወራራ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች ተፈናቅለዋል 9 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ ባሉበት ሆነው ለምግብ እህል እጥረት የተጋለጡ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በዛሬው እለት ያደረጉት ድጋፍ የተፈናቀሉና ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለመደገፍና ለማቋቋም ለሚደረገው ጥረት አስተዋጽኦ እንዳለው ገልፀዋል።

“ድጋፉ እርዳታ ለሚሹ ወገኖች በፍትሃዊነት እንዲደርስ ይደረጋል” ያሉት ኮሚሽነሩ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በድጋፍ ርክክቡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ አሸብር ባልቻ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳንኤል ተሬሳን ጨምሮ የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽነርና የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን የስራ ኃላፊዎች መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።