ለአሜሪካ የማዕቀብ ውሳኔ የኤርትራ ምላሽና ክስ

መስከረም 11/2014 (ዋልታ) ኤርትራ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መንግሥታት ባለሥልጣናት ላይ እንዲጣል ትዕዛዝ የሰጡበትን የማዕቀብ ውሳኔ ተቃወመች።

በአሜሪካ እና አውሮፓ አገራት የሚተላለፉ ሚዛን የሳቱ ውሳኔዎችንና የሚወሰዱ እርምጃዎችን የተቃወመው የኤርትራ መንግሥት አገራዊ ሕጎችን፣ የአገራትን ነፃነት እና ሉኣላዊነትን የሚጥሱ ስለመሆኑ በማሳወቅ ኮንኗል።

በማስፈራራት የሚመጣ ለውጥ አለመኖሩን አክሎም መሰል የአሜሪካ አካሄድ በርትዕ እና በሕግ ፊት ተቀባይነት የለውም ሲል የማዕቀብ ውሳኔውን እንደማይቀበል ማስታወቁን ቪኦኤ ዘግቧል።

በተያያዘ ዜና አሸባሪው ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀመው ጥቃት በሁሉም መመዘኛዎች ከፍተኛ ወንጀል መሆኑን የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ገልፀዋል፡፡

ሆኖም ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ አሸባሪው ሕወሓት የፈፀማቸውን ወንጀሎች እና የጦርነቱን ዋነኛ መነሻ ለመሸፋፈን የሐሰት ትርክቶችና ፕሮፖጋንዳዎችን አጠናክሮ መቀጠሉን በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡