ለአፍሪካ አገራት የጦር መኮንኖች ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ገለፃ ተደረገ

ሚያዝያ 12/2014 (ዋልታ) በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል አምባሳደር ፍስሃ ሻውል የኢትዮጵያን ሁኔታ በሚመለከት ከአምስት የአፍሪካ አገራት ለተውጣጡ የጦር መኮንንች ገለፃ አደረጉ።

የጦር መኮንኖቹ በታንዛኒያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ ስልጠና እየተከታተሉ ያሉ ሲሆን ከናይጄሪያ፣ ታንዛኒያ፣ ቡሩንዲ፣ ዝምባብዌና ሩዋንዳ የተውጣጡ መሆናቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

ለቡድኑ አባላት በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እና ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ገለፃ ያደረጉት አምባሳደር ፍስሃ ሻውል ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናት የተሻገረ የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ታሪክ እንዳላት አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በሁለትዮሽና በባለ ብዙ ወገን መድረኮች ያላትን ተሳትፎም አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።

በአሁን ጊዜ እየደረሰባት ያለውን ኢ-ፍትሃዊ ጫናዎች በሚመለከት ለጦር መኮንኖቹ አባላት ማብራሪያ የሰጡት አምባሳደሩ የሁላችንም እጣ ፈንታ ተመሳሳይ በመሆኑ ይሄን ድርጊት ለመቃወም አፍሪካዊያን በኅብረት መቆም አለብን ብለዋል።

የኅዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማንኛውንም የተፋሰሱ አገራት የማይጎዳ የልማት አጀንዳ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ውሃውን በሚመለከት ዘመን ያለፈበትን ኢ-ፍትሃዊ የቀኝ ገዢዎች ስምምነት በመተው የተፋሰሱ አገራት በትብብር መስራትና መጠቀም እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።