ለከተሞች በ10 ዓመታት ውስጥ 15 ሚሊዮን ምርታማ የስራ ዕድልን የመፍጠር ግብ ተቀመጠ

የከተሞችን ድህነትና ስራ አጥነትን ለመቀነስ በአስር ዓመታት ውስጥ 15 ሚሊዮን ምርታማና ተስማሚ የስራ ዕድልን የመፍጠር ግብ መቀመጡ ተገለጸ፡፡

የፌዴራል የከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በከተማ ልማት ሴክተር የአስር ዓመትና የአምስት ዓመት የልማት ዕቅድ ላይ በሀዋሳ ውይይት አካሄዷል፡፡

በሚኒስቴሩ የሚኒስትሯ ከፍተኛ አማካሪ አቶ ተስፋዬ ወ/ሚካኤል ለአስር ዓመት የተያዘው የዘርፉ ዕቅድ ዓላማው ከተሞችን የብልፅግና ማዕከላት ማድረግ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በገጠርና በከተማ የሚሰሩ የልማት ስራዎችን ማስተሳሰር፣ የሀገራዊ ምርት ድርሻን በ73% ማሳደግ እንዲሁም ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢን በ2022 ዓ.ም 4 ሺህ 689 ዶላር ማድረስ የዕቅዱ ዋንኛ ግቦች መሆናቸውን አቶ ተስፋዬ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም የከተሞችን ድህነትና ስራ አጥነት ለመቀነስ በአስር ዓመት ውስጥ 15 ሚሊዮን ምርታማና ተስማሚ የስራ ዕድልን ለመፍጠር ግብ ተጥሏል ብለዋል፡፡

ዕቅዱ የከተማ ነዋሪዎችን ኑሮ ከማሻሻል ረገድ ተስፋ ሰጪ መሆኑን የገለፁት የውይይቱ ተሳታፊዎች ለዕቅዱ ተግባራዊነት ከአደረጃጀት፣ ከግብዓት፣ ከክህሎትና ከቅንጅት አንፃር ተገቢውን ትኩረት በመስጠት መስራት እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡