ለውጭ መገናኛ ብዙኃን የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያን ከገንዘብ በላይ አገራቸውን እንዲያስቀድሙ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ጠየቀ

ኅዳር 2/2014 (ዋልታ) በውጭ መገናኛ ብዙኃን ተቀጥረው የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያን አገራቸው ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባትና ሉኣላዊነትን ከገንዘብ አስቀድመው እንዲሰሩ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዮናታን ተስፋ ከዋልታ ጋር ባደረጉት ቆይታ አሸባሪው ሕወሓት ብቻ ሳይሆን ከቡድኑ ጀርባ ያሉ የኢትዮጵያን እጅ በመጠምዘዝ አሁን ያለውን የአንድነት እና የመተባበር እሳቤ ለማጥፋት እንደማይተኙ መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በፊት የነበረው የመከፋፋል፣ ያለመተባባር እና ከፋፍሎ የመግዛት መርህ አሁን የለም ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ ጠላቶች ከምጣኔሃብት ጥገኝነት የምንላቀቅበትን አንድነታችንን አይፈልጉብትም ብለዋል፡፡

ለዚህም አንድነታችንን ስናጠናክር የውጭ እና የውስጥ ጫናዎች እንደሚበረቱ በመገንዘብ ኢትዮጵያዊነትን በማቀንቀን የጀመርነውን የብልጽግና ጉዞ አጠናክረን መቀጠል አለብንም ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ የራሷ ታሪክ፣ ፍልስፍና እና እሳቤ እንዲሁም አሸናፊ ሕዝብ ያላት ታላቅ አገር እንደመሆኗ ነው እየተፈተነች ያለችው ብለዋል፡፡

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ዮናታን ለዚህም የስነ ልቦና ዝግጅት ያሰፈልጋል ያሉ ሲሆን ለአገራችን ሉኣለዊነት፣ ለሕዝባችን ሰብኣዊ ክብር የሚፋለሙትን የመከላከያ ሰራዊት አባላትና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች መቀላቀል እና መደገፍ  ይገባል ብለዋል፡፡

አንዳንድ የግል መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በመዘንጋት ከመንግሥት የሚሰጡ አቅጣጫዎችንም ችላ ማለታቸውን አንስተዋል፡፡

ሕብረተሰቡን የማንቃት እና መረጃ የማድረስ ሃላፊነት እና ግዴታ አለባቸው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እነዚህ ተቋማት ግን የሚያስተላልፉት ከነባራዊ ሁኔታ የራቀ በአዘቦት ቀን የሚደረግ የመዝናኛና የሙዚቃ ድግስ ይመስላል ብለዋል፡፡ ሊታረም እንደሚገባውም አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡