ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመንግሥት አመራሮች በፌዴራሊዝምና ግጭት አስተዳደር ዙሪያ ስልጠና እየተሰጠ ነው

መጋቢት 27/2014 (ዋልታ) የሰላም ሚኒስቴር በፌዴራሊዝምና ግጭት አስተዳደር ዙሪያ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመንግሥት አመራሮች ስልጠና እየሰጠ ነው።
ስልጠናው በግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ፣ በግጭት አስተዳደርና አፈታት፣ በፌዴራሊዝም ፅንሰ ሀሳብና በመንግሥት ግንኙነት አዋጅ ላይ ትኩረት ባደረጉ ሀሳቦች ለክልል አመራሮችና ለ6ቱ ዞኖች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እየተሰጠ ይገኛል፡፡
የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አንድነት አሸናፊ በክልሉ የሚከሰቱ የግጭት፣ የመፈናቀልና የሞት ክስተቶች ውስብስብ ቢሆንም በዳበረ ስልጠና በመታገዝ ቀድሞ መተንበይ የሚችል አገልጋይ ባለሙያ የመፍጠር ሥራችንን በዚህ ስልጠና እናዳብራለን ብለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመንግሥት ዋና ተጠሪ ፀጋዬ ማሞ በበኩላቸው በክልሉ ያሉ ፀጋዎች በባለሀብቶች ዕይታ አግኝተው እንዲለሙ ሰላምን ማስፈን አስፈላጊ ሰለሆነ መንግሥት ጠንክሮ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በመድረኩ የተገኙት የሰላም ሚኒስትሩ አማካሪ ካይዳኪ ገዛኸኝ የፌዴራል ሥርዓቱ ሚዛኑን ጠብቆ እንዲሄድ የሰላም ዕሴትን ለመገንባት የሕዝቡን ግንዛቤ በበቂ መረጃ ማገዝ የሚችል ብቁ ባለሙያ ለማፍራት እንደ ሀገር የተለያዩ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ስልጠናው በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ ለሁለት ቀናት የሚሰጥ ስለመሆኑም ተገልጿል።
አክሊሉ ሲራጅ (ከሚዛን አማን)
ለፈጣን መረጃዎች፦
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!