ለግል አስጎብኝዎች እና የእግር ጉዞ አዘጋጆች የአቅም ግንባታና የስነምግባር ስልጠና እየሰጠ ነው

መጋቢት 11/2013 (ዋልታ) – ቱሪዝም ኢትዮጵያ ከስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ለግል አስጎብኝዎች እና የእግር ጉዞ አዘጋጆች የአቅም ግንባታና የስነምግባር ስልጠና እየሰጠ ነው፡፡

በአርባ ምንጭ ከተማ እየተሰጠ ባለው ስልጠና በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረው የቱሪዝም ልማትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም ካሰው ሀገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ ቱሪዝሙን ማልማት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ የግል አስጎብኚ ድርጅቶችና የእግር ጉዞ አዘጋጆች አቅም ለማሳደግ የአቅም ማጎልበት ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሰልጣኖቹ በሚኖራቸው የስልጠና ጊዜ በአርባ ምንጭ ከተማ ዙሪያ ያሉ የቱሪስት መስህቦች እንደሚጎበኙም ገልጸዋል፡፡

የስልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው፣ ስልጠናው መዘጋጀቱ ይበልጥ ለስራ እንዲነሳሱ እንደሚያደርጋቸው ገልጸው፣ ቱሪስቶች በሚኖራቸው ቆይታ ኢትዮጵያን እንዲወዷት የገጽታ ግንባታ እንሰራለን ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ 102 የግለሰብ አስጎብኝዎችና የእግር ጉዞ አዘጋጆች እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፣ አደረጃጀቶቻቸውን የመደገፍ ስራ እንደሚሰራ ተጠቁሟል፡፡

(በመማር ይበልጣል)