ለግጭት መከላከልና ሰብኣዊ መብት መከበር በቅንጅት ሊሠራ እንደሚገባ ተጠቆመ

ሚያዝያ 22/2014 (ዋልታ) በደብረ ብርሃን ከተማ የተለያዩ ሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች የተሳተፉበት ማኅበረሰብ ዐቀፍ የግጭት መከላከል፣ በቅድመ ግጭት ማስጠንቀቂያና ሰብኣዊ መብት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

መድረኩ በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ድርጅት የምሥራቅ አፍሪካ አካባቢያዊ ጽሕፈት ቤት በደብረ ብርሃንና አካባቢው ማስተባበሪያ የተዘጋጀ ሲሆን የሃይማኖት ተቋማት ፎረም ተወካዮች፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የሴቶች፣ የወጣቶችና የመምህራን ማኅበራት ተወካዮችና የሚዲያ አካላት ተሳትፈውበታል።

በምክክር መድረኩ በሀገሪቱ በየጊዜው በተለያዩ አካባቢዎች ብሔርንና ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው በሚቀሰቀሱ ግጭቶች ከፍተኛ የሆነ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች እየደረሱ እንደሆነ ተነስቷል።

ግጭቶችን አስቀድሞ ለመቆጣጠርና ለመከላከል ሲቪክ ማኅበራት ተቀናጅተው ሊሠሩ እንደሚገባ የማኅበራት ተወካዮች ገልጸዋል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ በግጭት መከላከልና ሰብኣዊ መብት ላይ የሚሠራ 14 አባላት ያሉት የሲቪክ ማኅበራት ጥምረት ኮሚቴ በመድረኩ ተመስርቷል።

ኮሚቴው ከሁሉም ሲቪክ ማኅበራትና ከመንግሥት የተለያዩ ተቋማት ጋር በመሆን ይሠራል ተብሏል።

የማስተባበሪያው የሰብኣዊ መብት ክትትል ባለሙያ ብሩክ ከበደ ድርጅታቸው ከተቋቋመው ኮሚቴና ከሁሉም ሲቪክ ማኅበራት አደረጃጀቶች ጋር እንደሚሠራ መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW