ለጎርጎራ ፕሮጀክት “የንጉሥ እራት” መርሃ ግብር በጎንደር ከተማ ሊዘጋጅ ነው

በገበታ ለሃገር ለተካተተው የጎርጎራ ፕሮጀክት አንድ ቢሊየን ብር የሚያስገኝ “የንጉሥ እራት” የተሰኘ መርሃ ግብር በጎንደር ከተማ እንደሚዘጋጅ የከተማዋ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ አስታወቁ።

በጣና ሃይቅ ዳርቻ የምትገኘው ጥንታዊቷ የጎርጎራ ከተማ ‘በገበታ ለሃገር ፕሮጀክት’ ከሚለሙ ሶስት ስፍራዎች መካከል እንደ መሆኗ፥ በክልሉ የሚገኙ ባለሃብቶች የሚታደሙበት “የንጉስ እራት” የተሰኘ መርሃ ግብር በጎንደር ከተማ በማዘጋጀት አንድ ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ እቅድ መያዙን ከንቲባው ተናግረዋል።

መርሃ-ግብሩ መቼ እንደሚከናወንና የአንድ እራት ዋጋ ተመን ስንት እንደሚሆን በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ የቱሪዝም ልማትን በማሳደግ ለሥራ እድል ፈጠራና የኢንቨስትመንት ፍሰትን በመጨመር ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የአካባቢው ማህበረሰብ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ጭምር ፕሮጀክቱን እንዲደግፍ የከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ከንቲባው ተናግረዋል።

በ”ገበታ ለሃገር” ፕሮጀክት ከጎርጎራ በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል ወንጪና በደቡብ ክልል የኮይሻ ፕሮጀክቶች እንደሚለሙ የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል፡፡