ለፀጥታ ኃይሎች የምናደርገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል- የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች

የወልዲያ ከተማ

ነሐሴ 25/2014 (ዋልታ) ”የሕወሓት የሽብር ቡድንን በጀግንነት እየተፋለሙ ለሚገኙ የመከላከያና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች የምናደርገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል’’ ሲሉ የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

በከተማው የንግድና ሌሎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ተገልጿል።

የከተማው ነዋሪዎች ”ወራሪ ቡድኑን ባጠረ ጊዜ ድል መምታት የምንችለው ከሰራዊቱ ጎን በመሰለፍ ነው” ያሉ ሲሆን ለመከላከያ ሰራዊቱና ሌሎች ፀጥታ ኃይሎች ጉልበት ለመስጠትም የእለት ደራሽ ምግቦችን በተደራጀ አግባብ እያዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል።

ተደራጅተው ስንቅ ለሰራዊቱ ግንባር ድረስ ሄደው ለማቅረብ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ገልጸው ከስንቅ ዝግጅት ባለፈ ግንባር በመግባት ጠላትን ለመዋጋት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የሕወሓት የሽብር ቡድንን በጀግንነት እየተፋለሙ ለሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች ደጀን መሆን እንደሚገባ የገለጹት የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች ይህ ድጋፍና እገዛም ሰራዊቱ ጦርነቱን በድል እስኪያጠናቅቅ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ሃሰተኛ ወሬን በስፋት በመጠቀም ኅብረተሰቡን ለማደናገር ይሰራል ያሉት ነዋሪቹ ለዚህም ኅብረተሰቡ የሽብር ቡድኑን የሃሰት ወሬ በመረዳት አካባቢውን ነቅቶ ሊጠብቅና ለሰራዊቱ ደጀንነቱን ሊያጠናክር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በወልዲያ ከተማ በአሁኑ ወቅት የጉሊት ገበያን ጨምሮ፣ ሌሎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንደቀጠሉ መሆናቸውን ኢዜአ ከስፍራው ዘግቧል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW