ለፌዴራል መንግስት ምስረታ ስኬታማነት የክልሉ መንግስት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል – አቶ አሻድሊ ሃሰን

መስከረም 23/2014 (ዋልታ) – ከፌዴራል መንግስትና ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን በአካባቢው የሚስተዋለውን የጸጥታ ችግር በመፍታት ለፌዴራል መንግስት ምስረታው ስኬታማነት ክልሉ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል ሲሉ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አሻድሊ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በአካባቢው የሚስተዋለውን የጸጥታ ችግር በመመከት የአዲሱን መንግስት ምስረታ ስኬታማ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።
በአካባቢው የተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ ፍላጎቶች አሉ፤ እስካሁን በአካባቢያችን ምርጫው ያልተካሄደውም በእነዚሁ ምክንያቶች ነው፤ በክልሉ ከሚገኙ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመስራት እንደመንግስትም እንደብልጽግና ፓርቲም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል ሲሉ ገልጸዋል።
በመተከልና በካማሺ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው።ነገር ግን በአካባቢው የውጭ ሃይሎች ፍላጎቶችም አሉበት።የሚመሰረተው አዲስ መንግስት በአገራችን ውስጥ የሚስተዋለውን የሰላምና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ሃላፊነት የሚጣልበት ይሆናልም ነው ያሉት።
በአካባቢው ያለውን ችግር ለማስተካከል ሰላም እንፈልጋለን፣ በአካባቢው ያለውን ችግር እናስተካክላለን ከሚሉ አካላት ጋር ሲደረግ የነበረው ሰላም የማስፈን ስራም ይቀጥላል ብለዋል።