ለ3 ወራት የሚቆይ ድጋፍ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር እየተካሄደ ነው

ሚያዝያ 18/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን እና የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኤልሻዳይ ኢንተርቴመንት ጋር ከተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቀሉና በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የሚውል ድጋፍ እየተካሄደ መሆኑን አስታወቀ።
የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብሩ ከሚያዝያ 1 ጀምሮ እየተሰበሰበ ሲሆን እስከ ሰኔ 30 ለሦስት ወራት የሚቆይ እንደሆነም ተጠቁሟል።
ድጋፉ በሰሜኑ ጦርነት እና በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች ድጋፍ ማድረግን ዓላማ ማድረጉ ተጠቁሟል፡፡
በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ተሳትፎና ንቅናቄ ማስፋፊያ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ሀብታሙ ከበደ በሦስት ወራት ውስጥ እስከ 500 ሚሊየን ለማሰባሰብ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ወጣቶች ለሀገር ሰላምና ደኅንነት መጎልበት እየሰሩ ያለው ሥራ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ፅጌሬዳ ዘውዱ በበኩላቸው ወጣቶች ሰላምን ለማስፈን ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራው ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር ይሰራል ብለዋል።
በተጨማሪም በሁሉም ክልሎች ሩጫዎችን በማካሄድ ከቲሸርት ሽያጭ የሚገኘውን ገቢ በጦርነቱና በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የሚውል እንደሆነም ገልፀዋል።
በሱራፌል መንግሥቴ
ለፈጣን መረጃዎች፦
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!