ለ40 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ

መስከረም 2/2014 (ዋልታ) የአፋር ክልል መንግሥት አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ለ40 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ።

የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ነሙሳ ያሲን ለኢዜአ እንደገለጹት በይቅርታ ቦርድ ተመርምሮ መስፈርቱን አሟልተው ለተገኙ ታራሚዎች ይቅርታው ተደርጓል።

“ይቅርታ ከተደረገላቸው ታራሚዎች መካከል በፈፀሙት ወንጀል የተፀፀቱ፣ አብዛኛውን የእስር ጊዜያቸውን የጨረሱ፣ በዕድሜያቸው የገፉና የጤና ዕክል ያጋጠማቸው ይገኙበታል” ብለዋል።

ሆኖም በሙስና፣ በአገር ክህደትና ተያያዥ ከፍተኛ ወንጀሎች የፍርድ ውሳኔ የተሰጣቸው ታራሚዎች በይቅርታው አልተካተቱም ነው ያሉት።

የይቅርታው ተጠቃሚ የሆኑት 40 ታራሚዎች ከያሉቧቸው ማረሚያ ቤቶች ከመስከረም 1/2014 ጀምሮ እንዲወጡ እየተደረገም ነው።