ለ650 አቅመ ደካማ ወገኖች የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ተካሄደ

መጋቢት 25/2014 (ዋልታ) በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የታላቁን ረመዳን ወር ጾም ምክንያት በማድረግ ለ650 አቅመ ደካማ ወገኖች የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ተካሄደ።
በመርሃ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሀቢባ ሲራጅ፣ የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፍቃድ ኮሚሽን ኮሚሽነር አስፋው ተክሌ እና ሌሎች አመራሮች ተገኝተዋል።
ለ650 አነስተኛ ገቢ ላላቸው የተለያየ መጠን ያላቸው የምግብ ግብዓቶችን 1 ነጥብ 62 ሚሊዮን ብር በሚገመት ድጋፍ ተደርጓል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መለሰ ዓለሙ እንደተናገሩት በተለያየ ምክንያት አነስተኛ ገቢ ያላቸው አሁን ባለው የኑሮ ውድነት ችግሩ ከፍተኛ እንደሆነና ከችግሩ ለመላቀቅ ሕዝብና መንግሥት በጋራ በመሆን የኑሮ ውድነት የሚያባብሱ ምክንያቶችን መከላከል ይገባል።
በከተማ ደረጃ ለ300 ሺሕ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ማዕድ ለማጋራት የታቀደ ሲሆን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በወሩ ውስጥ ለ37 ሺሕ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች ማዕድ ማጋራት እንደሚደረግ ከአዲስ አበባ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።