ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከል ማስጀመሪያ መርኃ-ግብሩን እያካሄደ ነው

ግንቦት 4/2014 (ዋልታ) የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከል ማስጀመሪያ መርኃ-ግብሩን እያካሄደ ይገኛል።

በመክፈቻ መርኃ-ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ተወካይ ጄይላን ውልይ (ፕ/ር) ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው ዜጎች ስለ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ለዓለም ለማሳወቅ እንደሚረዳም ተናግረዋል።
ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ዘርፈ ብዙ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራ እየሰራ መሆኑን አንስተው ፐብሊክ ዲፕሎማሲ በትምህርት የታገዘ እንዲሆንም እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ይህ ማዕከል ኢትዮጵያ ለምታካሂደው የዲፕሎማሲ ሥራ የተለያዩ ግብዓቶችን እንደሚያቀርብም ነው የገለፁት።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለመጉዳት ጥረት የሚያደርጉ አካላት እንዳሉ የገለፁ ሲሆን ይህንን ጫናዎች ለመቀነስ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ እየተቋቋመ የሚገኘው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከል የኢትዮጵያን ነባራዊ ሀቅ ለዓለም ለማስረዳት ሚናው የጎላ እንደሆነም ተናግረዋል።
ሱራፌል መንግስቴ (ከሐረማያ)