ሐራምቤ ዩኒቨርሲቲ አቅመ ደካማ እናቶችን በመደገፍ የሴቶች ቀንን እያከበረ ነው

የካቲት 29/2014 (ዋልታ) ሐራምቤ ዩኒቨርሲቲ ዓለም ዐቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ለአቅመ ደካማ እናቶች ድጋፍ አድርጓል፡፡

ሴቶች በቀደምት ጊዜያት ተጭኖባቸው የነበረውን ጫና ተቋቁመው ለዓለም ያበረከቱት አስተዋጽኦ የላቅ በመሆኑ ቀኑ ሲከበር በማኅበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ሴቶችን ድጋፍ እና አለኝታነትን በማሳየት መሆን እንዳለበት የሐራምቤ ዩኒቨርሲቲ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፈይሳ አራርሳ ገልጸዋል፡፡

ዓለም ለሴት የተዘጋውን መድረክ እየከፈተ ባለበት በዚህ ወቅት ሐራምቤ ዩኒቨርሲቲም ከ60 በመቶ በላይ ለሚሆኑ ሴት ተማሪዎች ቅድሚያ በመስጠት ብቁ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም የጾታ እኩልነት ሚዛን የተዛባባቸው እና ለሴቶች የተዘጉ መድረኮችን ለመክፈትም የሁሉም አካል ርብርብን የሚጠይቅ መሆኑ ተመላክቷል::

በሔብሮን ዋልታው