ሕብረ ብሔራዊ የፌዴራል ስርዓቱ በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ እንዳልነበረ ተገለጸ

ግንቦት 14/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ ሕብረ ብሔራዊ የፌዴራል ስርዓት ተግባራዊ ቢደረግም በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ እንዳልነበረ ተገለጸ።

“ፌዴራሊዝም፣ ሠላምና ልማት በኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሃሳብ በሠላም ሚኒስቴር የተዘጋጀው አገራዊ ኮንፈረንስ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አደም ፋራህን ጨምሮ ከከፍትኛ የትምህርት ተቋማት፣ ከጥናት ኢንስቲትዩቶችና ከመንግስት ተቋማት የተውጣጡ 65 ተሳታፊዎችና ጥናት አቅራቢዎች ተታድመዋል።

አፈ ጉባዔ አደም ፋራህ በኢትዮጵያ ሕገመንግስቱ ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ ሕብረ ብሔራዊ የፌዴራል ስርዓት ተግባራዊ መደረጉን ገልጸው፤ ይሁን እንጂ በተለይ ከአገራዊ ለውጡ በፊት በነበሩት መሰናክሎች የፌዴራል ስርዓቱ በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ እንዳልነበረ ተናግረዋል።
በሂደት ካጋጠሙ ተግዳሮቶች መካከል የዴሞክራሲ ባህልና አሰራር አለመዳበር፣ ኢትዮጵያዊ የጋራ ማንነትና እሴቶች በሚገባ አለመጎልበትና ፌዴራላዊ አስተሳሰብ አለመኖር ይገኙበታል።

የፖለቲካ ባሕል፣ አመራርና እሴቶች በሚገባ አለመዳበር እንዲሁም ኢትዮጵያን የሚመስሉ ሀገራዊ ተቋማት አለመፈጠርም ተጨማሪ ምክንያት መሆናቸውን ገልጸዋል።

የዜጎች እኩልነት መብት በተሟላ መልኩ አለመከበርና የተመጣጠነ እድገት ለማረጋገጥ የሚያስችል አሰራር አለመዘርጋት የፌዴራል ስርዓቱ አተገባበር እንከኖች እንደነበሩ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ በወቅቱ ሕገ መንግስታዊ ምላሽ እንዳላገኙ ያወሱት አፈ ጉባዔው፤ የክልል መንግስታት ግንኙነት ስርዓት አለመኖሩም ሌላው ክፍተት ነበር ብለዋል።

በሠላም ሚኒስቴር የፌዴራሊዝምና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ ሕገ መንግስታዊ ሆኖ በተተገበረባቸው ዓመታት አንጻራዊ ለውጦች ቢያስመዘግብም ጉድለቶች እንደነበሩ ነው የገለጹት።

በብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የቋንቋ፣ የባህልና ሌሎችም ማንነቶች እድገት ላይ የፌዴራል ስርዓቱ በጎ ሚና መጫወቱን ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ ከአስተዳደርና ሌሎች የግልና የቡድን መብቶች ማስከበር አኳያ ክፍተቶች እንደነበሩ ያስታወሱት ዶክተር ስዩም፤ “ባለፉት ሦስት ዓመታት ችግሮችን ለማስተካከል ሪፎርም ተደርጓል” ብለዋል።

አሁንም ቢሆን የ”እኔ” እና የ”እኛ” የሚል አስተሳሰብ “የፈጠረው የገመድ ጉተታ በአገሪቱ ያለውን ቅራኔ እንዲቀጥል” ማድረጉን ገልጸው፤ የምሁራን ድምጽ መዳከምና የሰፈር ተንታኞች መበራከት አባባሽ ምክንያቶች መሆናቸውንም ነው ዶክተር ስዩም ያመለከቱት።

በመሆኑም “በሀገራችን የሕብረ ብሔራዊ ፌዴራል ስርዓቱ አተገባበር ላይ የምሁራን ሚና ሊዳብር” ይገባል ብለዋል።

በተለይ አገር በቀል እውቀቶችን አጉልቶ በማውጣት ዘላቂ መፍትሄ በመዘርጋት ሂደት ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል ማቅረባቸውን ኢዜአ ገልጿል።