ሕወሓት ህዝቡን ለጦርነት መቀስቀሱ ድርጅቱ በጦርነት አዙሪት ውስጥ የመኖር ፍላጎት እንዳለው ማሳያ ነው ተባለ

ግንቦት 12/2014 (ዋልታ) “ሕወሓት ቀደም ሲል በተደረገው ጦርነት ከጉዳቱ ሳያገግም ለሌላ ጦርነት ራሱን ማዘጋጀቱ የእብደቱ ሁኔታ ከፍተኛ ደረጃ መድረሱን ያመላክታል ሲሉ የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ተናገሩ።

ቀደም ሲል ሕወሓት በለኮሰው ጦርነት በሁለቱም ወገን በተለየ መልኩ ደግሞ የትግራይ ወጣት ላይ የደረሰውን ጉዳት ግምት ውስጥ ሳያስገባ እንደገና ህዝቡን ለጦርነት መቀስቀሱ ድርጅቱ በጦርነት አዙሪት ውስጥ የመኖር ፍላጎት እንዳለው ማሳያ ነው።

እንደ ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ ሕወሓት እያደረገ ያለው የጦርነት አዋጅ አቅም ኖሮት እንደገና በሀይል ወደ ስልጣን ለመመለስ ሳይሆን በብዙ መልኩ እየተነፈገ ያለውን የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ትኩረት ለመሳብ ነው።

ቡድኑ በሴራና በድራማ የተካነ በመሆኑ እንደ ልማዱ ጦርነት በመጫር መንግሥት ያልተመጣጠነ እርምጃ በንጹሀን ዜጎች ላይ እንደወሰደና ሰብዓዊ ቀውሶች እንደተፈጠሩ አድርጎ የአለምን ህዝብ ለማሳሳት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ነው።

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ በፊት ከነበረው ሁኔታ በመማር “እውነት ነጻ ያወጣኛል” የሚለውን እሳቤውን በመቀየር የቡድኑን ሴራ የሚመጥን ስራ መስራት ይጠበቅበታል ያሉት ሊቀመንበሩ ከዚህ አንጻር እውነት መያዝ ብቻ ለአሸናፊነት ስለማያበቃ ለኢትዮጵያ የሚሟገቱ ወገኖች ማብዛትና ማሰለፍ ጠቃሚ መሆኑን መክረዋል።

ከዚህ በፊት ሕወሓት የአሜሪካ ከፍተኛ አመራሮች ሳይቀር በገንዘብና በአይነት በመግዛት ውሸትን እንደ እውነት በማስተጋባት ተሳክቶለታል እንደነበር አስታውሰዋል።

ዳሩ ግን ከጊዜ ቆይታ በኋላ የአለም ሚዲያና የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች በክልሉ በመግባት ባደረጉት ምርመራና ምልከታ ውሸት ራቁቷን ቀርታለች ሲሉ ማብራራታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

እንዲያውም ቡድኑ በአለም አቀፍ ደረጃ በሚወጡ አንዳንድ ሪፖርቶች ደስተኛ አለመሆኑን ሲገልጽ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡