ሕወሓት ከግብጽና ሱዳን ጀነራሎች ጋር በመሆን ዳግም ጦርነት ለመጀመር እየሰራ መሆኑ ተጋለጠ

ግንቦት 26/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ሕወሓት ከአንዳንድ የግብጽና ሱዳን ጀነራሎች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት ለመጀመር እየሰራ መሆኑን የቀድሞ የአውሮፓ ዲፕሎማት አጋለጡ።
አሸባሪው ሕወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ በማካሄድ ከፍተኛ ውድመት ፈጽሟል፡፡
የኢትዮጵያን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉትና በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር የነበሩት ሲሞ ፓርቪያነን በከፍተኛ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ላይ የሚገኘው ሕወሓት ሌላ ጦርነት ለመክፈት ከግብጽና ሱዳን ድጋፍ እየፈለገ ይገኛል ብለዋል፡፡
በዚህም በተለይ አንዳንድ የካይሮና ካርቱም ጀነራሎች ከአሸባሪው ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ለማዳከም እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አሸባሪው በርካታ ቁጥር ያላቸው ታጣቂዎቹን በአፋርና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች እያሰፈረ መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡
እንደ ዲፕሎማቱ ገለጻም የሽብር ቡድኑ ለሌላ አውዳሚ ጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን የሚያመላክቱ በርካታ አስረጂዎች አሉ፡፡
የሽብር ቡድኑ በስፋት ታጣቂዎችን ከመመልመል ባሻገር ከአንዳንድ የግብጽና ሱዳን ጀነራሎች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ውስጥ አለመረጋጋትን ለመፍጠር እየሰራ ነው፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተቀመጠለት እቅድ እየተከናወነ መሆኑ ደግሞ ውጫዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ከሽብር ቡድኑ ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ አድርጓል ነው ያሉት፡፡
ምንም እንኳ ግድቡ አሁን ላይ ኃይል መስጠት ቢጀምርም ግብጽና ሱዳን ከአንዳንድ ምዕራባዊያን የሚያገኙትን ድጋፍ በመጠቀም በግድቡና በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ላይ ያላቸውን ዓላማ ለማስፈጸም እየሰሩ መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡
እንደ ዲፕሎማቱ ገለጻ የወልቃይት ጠገዴ ኮሪደር አሸባሪው ሕወሓት ከግብጽና ሱዳን ድጋፍ ለማግኘት እጅጉን የሚፈልገው ስትራቴጂካዊ አካባቢ ነው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን ይህን በመገንዘብ ነቅተው ሊቆሙ እንደሚገባ ነው ለኢዜአ የተናገሩት፡፡
ቡድኑ ለሰብዓዊ ድጋፍ ተብሎ ወደ ትግራይ ክልል የሚገቡ ተሽከርካሪዎችና ሌሎች ቁሳቁሶችን ለጦርነት እንደሚጠቀምም አንስተዋል፡፡
አሸባሪው ቡድን የኢትዮጵያን ኅልውና የማይፈልጉ ጠላቶች ተላላኪ መሆኑን በተግባር እያሳየ እንደሚገኝ አንስተው ነገር ግን ኢትዮጵያ የትኛውንም ሴራ የመመከት አቅም እንዳላት እምነቴ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር የነበሩት ሲሞ ፓርቪያነን ኢትዮጵያ ለምዕራባዊያን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላት አገር መሆኗን በማንሳት አገራትቱ በኢትዮጵያን ያለውን ትክክለኛ ሁኔታ በመገንዘብ ሊደግፏት ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡