ሕዝቡ ሀገሩን ለማዳን ማንኛውንም መስዋእትነት እንደሚከፍል በተግባር አሳይቷል – የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት

ጥቅምት 28/2014 (ዋልታ) የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሕዝቡ ሀገሩን ለማዳን ማንኛውንም መስዋእትነት እንደሚከፍል በተግባር አሳይቷል ሲል ገለጸ፡፡
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በወቅታዊ ጉዳይ ያስተላለፈው ሙሉ መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል፡-
ሰሞኑን በተለያዩ ክልሎች ከ30 ሚልዮን በላይ ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ ስለሀገሩ ተናግሯል። ኢትዮጵያን ለማዳን እስከ ሕይወት መስዋእትነት እንደሚከፍል፣ ለጸጥታ ኃይሉ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ፣ ማንኛውንም የውጭ ጣልቃ ገብነት እንደማይቀበል፣ የሕወሓትንና አጋር ጽንፈኛ ኃይሎችን ሀገር የማፍረስ የሽብር ተግባራት አጥብቆ እንደሚያወግዝ በግልጽ ተናግሯል።
አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች፣ ዲፕሎማቶችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ስለ ኢትዮጵያ የሚያስተላልፉትን የተዛባ መረጃ ሕዝቡ ኮንኗል። የሚያስተዳድረውን መንግሥት ነጻ፣ ገለልተኛና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መምረጡንና ይህንን ውሳኔውንም ዓለም እንዲያከብርለት ሕዝቡ አጥብቆ ጠይቋል።
ሕዝቡ ሀገሩን ለማዳን ማንኛውንም መስዋእትነት እንደሚከፍል በተግባር አሳይቷል።
ሕዝቡ በወራሪው በተያዙ አካባቢዎችም በከፍተኛ ግለት እየተነሣ ነው። በተወረሩ አካባቢዎች የሚገኘው ሕዝብ ጽንፈኛውን ሕወሓት ምቾት ተሰምቶት እንዳይቀመጥ እያደረገው ይገኛል። ይህ የሕዝብ ንቅናቄ አሸባሪውን በሁሉም ቦታዎች እግር በእግር እየተከታተለ ርምጃ በመውሰድ አካባቢዎችን ተገድዶ እንዲለቅ እያደረገው ይገኛል።
አሁን የተጀመረውን ለኢትዮጵያ ህልውና ሕዝብን የማዝመት ንቅናቄ በብዛትና በስፋት በማከናወን፣ አሸባሪውን ሕወሓትን ድል ማድረግ እንዳለበት ሕዝቡ በአንድ ቋንቋ ተናግሯል። ግንባር ቀደም ኾኖ እንደሚዘምትም አረጋግጧል። ወሳኙ ጉዳይ የውስጥ አቅማችንን መጠቀም መሆኑን ሕዝቡ በዐደባባይ አሳይቷል።
ሕዝብ ተናግሯልና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሊያዳምጥ ይገባል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት