ሕገወጥ የነዳጅ ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር የሚያስችል ጠንከር ያለ መመሪያ ተዘጋጀ

ግንቦት 17/2014 (ዋልታ) ነዳጅ በሕገወጥ መንገድ ወደ ሌሎች አገራት የሚያሻግሩትን ለመቆጣጠር ጠንከር ያለ መመሪያ ማዘጋጀቱን የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

በተደጋጋሚ የሚስተዋለውን ሕገወጥ የነዳጅ ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ለመከላከል እና ጠበቅ ያለ እርምጃ ለመውሰድ የአዲስ መመሪያ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የሚኒስቴሩ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ቁምነገር እውነቱ ገልጸዋል።

መንግሥት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወደ አገር የሚያስመጣውን ነዳጅ በሕገወጥ መንገድ ወደ ሌሎች አገራት የሚያሻግሩ አካላትን መቆጣጠር ጊዜ የማይሰጠው መሆኑን ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።

መንግሥት የነዳጅ ምርትን ከውጭ በማስገባት በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ቢሆንም፣ በአንዳንድ ድንበር ከተሞች ከመጠን ያለፈ የነዳጅ ማደያዎችን በመክፈት በውድ የገባውን የነዳጅ ምርት ወደ ሌሎች አገራት በማስተላለፍ አገሪቱን ጥቅም እያሳጡ እንደሆነም ነው ዳይሬክተሯ ያብራሩት።

በአዲሱ መመሪያ መሰረት ነዳጅ ከመነሻው ወደብ እስከ መዳረሻው ድረስ ጥብቅ የሆነ የጂፒኤስ የስርጭት ክትትል ሥርዓት መተግበር፣ ማደያ የሌለባቸውን ከተሞች እና አካባቢዎች ምክንያት በማድረግ የሚሰጠውን የችርቻሮ ንግድ ፈቃድ አሰጣጥን ማረም፣ እንዲሁም የነዳጅ ኩባንያዎች በቀጥታ ተገኝተው ለሚጠቀሙ ተቋማት የፈቃድ አሰጣጥን ለማስተካከል የተዘጋጀ ነው ብለዋል።

በሕገወጥ ኮንትሮባንድ ንግድ ላይ እስካሁን በተወሰደው እርምጃ ለውጥ ማምጣት ባለመቻሉ ጠንከር ያለ መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መግባት ማስፈለጉን ነው የተናገሩት።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም ከዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ለመቋቋም መንግሥት በድጎማ ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ መሆኑ ዳይሬክተሯ አክለዋል ሲል የዘገበው ኢቢሲ ነው።