መላ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት አገርን እየታደጉ የሚገኙበት ወቅት ላይ የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ልዩ ትርጉም አለው ተባለ

ኅዳር 22/2014 (ዋልታ) ለ15 ዓመታት በተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ሲከበር የቆየው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ዘንድሮ “ወንድማማችነት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል በተለየ መልኩ እንደሚከበር የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዛህራ ሁመድ አስታውቀዋል።

የዘንድሮው 16ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አስተናጋጅነት በድምቀት እንደሚከበር ምክትል አፈ ጉባኤዋ ገልጸዋል።

የዘንድሮን በዓል የተለየ የሚያደርገውም ኢትዮጵያ በውስጥ አሸባሪ ኃይሎችና በውጭ ኃይሎች የተባበረ ጥቃት የኅልውና አደጋ በተጋረጠባት በዚህ ሰዓት ሁሉም ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአንድነት በመቆም አገርን እየታደጉ የሚገኙበት ወቅት ላይ የሚከበር መሆኑ ነው ተብሏል፡፡

አሸባሪው የትሕነግ ቡድን ከውጭ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቅድሚያ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን መደምሰስና መበተን በሚል እቅድ በሰሜን ዕዝ ላይ መቼም ታይቶ በማይታወቅ ክህደት ጀምላ ጭፍጨፋ ማካሄዱን ያስታወሱት ምክትል አፈ ጉባኤዋ በዚህም ሳይወሰን የችግሩ ገፈት ቀማሽ በሆነው በወንድሞቹ የአፋርና የአማራ ሕዝቦች ላይ ታሪክ መቼም ይቅር የማይለውን የዘር ማጥፋት ወንጀሎች መፈፀሙን ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳ በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን እልህ አስጨራሽ የሕልውና ዘመቻ ላይ ብትሆንም አሃዳዊያን ናችሁ በማለት ኅብረብሔራዊ የዴሞክራሲ ሥርዓታችንን ለማጠልሸት የሚሯሯጡ ጠላቶቻችንን አንገት ለማስደፋትና የብሔር፣ የብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ቃል ኪዳን እንደገና ለማደስ በዓሉ በድምቀት ይከበራል ነው የተባለው፡፡

በዚህም መሰረት በዓሉ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በፓናል ውይይት እንደሚከበርና ክልሎችም በማዕከል በተዘጋጀላቸው ወቅታዊ የመወያያ ሰነዶች አማካይኝነት እስከ ቀበሌ ድረስ በማውረድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በመስጠት በዓሉን እንደሚያከብሩ ተገልጿል፡፡

የፌዴራልና የክልል የሲቪል ሰርቪስ ሁሉም ሰራተኞች፣ መምህራን፣ ተማሪዎችና  የየዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ፣ የሴቶችና የወጣቶች አደረጃጀቶች በሚቀርቡላቸው ሰነዶች ላይ ውይይት በማድረግ በዓሉን እንደሚያከብሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ለሰራዊቱ ደም በመለገስ እንዲሁም ለተፈናቀሉ ወገኖች፣ በግንባር እየተፋለም ላለው የአገር መከላከያ ሰራዊትና የዘማች ቤተሰቦች ድጋፍ ማድረግ የብዓሉ መርኃግብር አካል መሆኑ ተመላክቷል።

በደምሰው በነበሩ