መርማሪ ቦርዱ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈፃፀም ተመለከተ

ታኅሣሥ 23/2014 (ዋልታ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በመገኘት አዋጁን ተላልፈዋል በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች ሰብኣዊ አያያዝን ተመለከተ፡፡

የቦርዱ አባላት በከተማ አስተዳደሩ ስር በሚገኙ ከዚራ፣  ሳቢያን እና  አዲስ ከተማ ፖሊስ ጣቢያዎች በመገኘት ተጠርጣሪዎች ያረፉባቸውን ቦታዎች ተመልክተዋል፡፡

ከየማረፊያ ቤቱ ከተውጣጡ የተጠርጣሪ ተወካዮች ጋር በሰብኣዊ አያያዝ፣ በውሃ፣ ምግብ፣ ህክምና እና በመፀዳጃ ቤትና የንፅህና መጠበቂያ አቅርቦት ዙሪያም በተናጠል አወያይቷል፡፡

በተመሳሳይም ቦርዱ ከከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ፣ ከፖሊስ ኮሚሽነርና ሌሎችም በየደረጃው ካሉ የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

ከውይይቱ በኋላም ቦርዱ የከተማ አስተዳደሩ አዋጁን ተፈጻሚ ለማድረግ ያከናወናቸውን ጠንካራ አፈጻፀሞች እና በቀጣይ ቢታዩ ተብለው የተለዩ ነጥቦችን በሰጠው የማጠቃለያ ግብረ መልሶች አመላክቷል፡፡

በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች በብሄር ሳይሆን ድርጊት ተኮር ላይ ብቻ መሆኑ፣ የበርካታ ተጠርጣሪዎች መዝገብ በአግባቡ ተደራጅቶ ወደክስ ሄደት ለመግባት ዝግጅት መደረጉን፣ ስጋት የማያሳድሩ፣ እድሚያቸው የገፋና ህመም ያለባቸው ተጠርጣሪዎች ተጣርቶ መለቀቅ መቻላቸው ቦርዱ በጥንካሬ ካስቀመጣቸው ውስጥ እንደሚገኙበት ተጠቁሟል፡፡

የምርመራ ሂደትን በማፋጠን ጥፋተኛ የሆኑትንና ያልሆኑትን የመለየት፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚገናኙበትን ሁኔታ የማመቻቸት፣ በአንዳንድ ማረፊያ ቦታዎች ላይ የሚታየውን ጥበት ተመልክቶ የሚስተካከልበት ሁኔታ ቢፈጠር የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡