መንግሥት ሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ሰኔ 27/2014 (ዋልታ) መንግሥት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራ እንዲሳካ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባለፉት አራት ወራት ባከናወናቸው ሥራዎች ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መክሯል።

ሀገር እንድትረጋጋ እና ስርዓት ባለው መንገድ እንድትመራ እንዲሁም ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ትልቅ ትልም ይዞ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ ለመወጣት ጥሩ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

መንግሥት በኮሚሽኑ ሥራ ጣልቃ የመግባት ፍላት የለውም ያሉ ሲሆን እንደማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ተሳትፈን የውጤቱ ተካፋይ ለመሆን ነው ፍላጎታችን ብለዋል።

ስለሆነም ኮሚሽኑ የሚፈልገውን ድጋፍ ለማድረግ መንግሥት ቁርጠኛ ነው ሲሉ ገልፀዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ኮሚሽኑ ባለፉት አራት ወራት በእቅዱ መሠረት ተጨባጭ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡

በዚህም ቀሪ ሥራዎችን እስከ መስከረም ድረስ በማጠናቀቅ የምክክር ሂደቱ በተያዘለት ጊዜ ለማካሄድ ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል።

በአስታርቃቸው ወልዴ