መንግሥት በአሸባሪው አልሸባብ ላይ እየተወሰደ የሚገኘው የተቀናጀ እርምጃ በአኩሪ ድል ታጅቦ ቀጥሏል አለ

ሐምሌ 20/2014 (ዋልታ) በአሸባሪው የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን ላይ እየተወሰደ የሚገኘው የተቀናጀ እርምጃ በአኩሪ ድል ታጅቦ መቀጠሉን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
በአሸባሪው የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን ላይ እየተወሰደ የሚገኘው የተቀናጀ እርምጃ በአኩሪ ድል ታጅቦ ቀጥሏል!
ከቀናት በፊት “አቶ” በሚባለው ቦታ ወደ ሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን ገብቶ በነበረው የአሸባሪው አልሸባብ ታጣቂ ቡድን ላይ በተወሰደው እርምጃ አብዛኛው የቡድኑ አባላት ሲደመሰሱ ሸሽተው ተደብቀው የነበሩ 25 የሽብር ቡድኑ አባላት ላይም እርምጃ ተወስዷል።
በደረሰበት የተቀናጀ የማጥቃት እርምጃ የተበተነው ጥቂት ሃይልም የያዘውን ከባድ መሳሪያ መጨረሱንና ባገኘበት ቦታ ለመደበቅ እየሞከረ ይገኛል። እስካሁንም የሽብር ቡድኑ ይዞት ከመጣው 4 የረጅም ርቀት መገናኛ ሬዲዮ ውስጥ ሶስቱ ተማርከዋል።
ፌርፌር በተባለው አካባቢ በኩል ገብቶ ከነበረው የሽብር ቡድኑ ታጣቂ ውስጥም በ85ቱ ላይ እርምጃ ተወስዶ ሸሽተው ወደመጡበት ሲመለሱ በነበሩትም ላይ የጎረቤት ሃገር ሶማሊያ ፌደራል ሃይል የማያዳግም እርምጃ ወስዶባቸዋል።
እስካሁንም ድንበር ጥሶ ከገባው ታጣቂ ሃይል ውስጥ ከ209 በላይ የሚሆኑት በክልሉና በፌደራል የጸጥታ ሃይሉ የተቀናጀ እርምጃ መደምሰሳቸው ታውቋል። በክልሉ ህዝብና ሚሊሻ እርምጃ የተወሰደበትና የተማረከውን የሽብር ቡድኑ አባላት ትክክለኛ ቁጥርም እየተጣራ ይገኛል።
የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ በሶማሌ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የሞከረው የአልሸባብ አሸባሪ ቡድን በክልሉ ልዩ ሃይል አኩሪ ተጋድሎና በፌደራል የጸጥታ ሃይሎች የተቀናጀ ጥረት ከፍተኛ የሰው ሃይልና የንብረት ኪሳራ ደርሶበታል።
ይህ የሽብር ቡድን በኤልከሬ ወረዳ አልፎ ወደ ኦሮሚያ ክልል በመግባት ከሌላኛው የሽብር ቡድን ከሸኔ ጋር ለመገናኘት አልሞ የነበረ ቢሆንም ይህ እቅዱ ሙሉ በሙሉ መክሸፉ ተረጋግጧል።
በተቀናጀው የመልሶ ማጥቃት የተበታተነውና ተቆርጦ የቀረውን የሽብር ቡድኑ ሃይል ላይ የሚወሰደው የማጽዳት ተልእኮ በተቀናጀና በተናበበ መልኩ ይቀጥላል።
የሽብር ቡድኑ ይዞት የመጣውን የሽብር ተልእኮ ሙሉ በሙሉ በማክሸፍና አሁንም ገብቶባቸው ከነበሩት አካባቢዎች በማጽዳቱ ሂደት ከጸጥታ ሃይሉ ባሻገር የአካባቢው ህዝብ አስተዋጽኦና መስዋእትነት ከፍተኛ የነበረ ሲሆን ይህ ቡድን ሙሉ በሙሉ ተደምስሶ እስኪጠናቀቅም ህዝቡ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መንግስት ጥሪውን ያቀርባል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት