መንግሥት በየቀኑ 10 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ ወደ ሀገር ውስጥ እያስገባ መሆኑ ተጠቆመ

ሳህረላ አብዱላሂ

ሰኔ 28/2014 (ዋልታ) መንግሥት በየቀኑ በአማካይ 10 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ ወደ ሀገር ውስጥ እያስገባ መሆኑን የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ገለጸ።

ባለስልጣኑ በሐምሌ ወር በነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ይኖራል በሚል ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የምጣኔ ሃብት አሻጥር የሚፈጥሩ አካላት ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድም አሳስቧል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሳህረላ አብዱላሂ እንዳሉት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከባለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ የተከሰተው የነዳጅ እጥረት መንስኤ አቅርቦት ሳይሆን በሥርጭት ላይ በሚፈጸሙ ችግሮች እንደሆነ ተረጋግጧል።

ቀደም ሲል በየወሩ መጨረሻ ቤንዚን ላይ እጥረት ይከሰት እንደነበር ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት ባልተለመደ ሁኔታ በናፍጣ ላይ የተከሰተው እጥረት የሀገርን ሃብት ለግል ጥቅም ለማዋል የተደረገ አሻጥር መሆኑን ተናግረዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ በባለፉት ሦስት ወራት መረጃ መሰረት ከጂቡቲ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው የነዳጅ አቅርቦት በየወሩ እየጨመረ ነው ብለዋል።

በዚህም መንግሥት በአሁኑ ወቅት በየቀኑ በአማካይ 10 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ ወደ ሀገር ውስጥ እያስገባ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ ቦታዎች ቆመው የነዳጅ እጥረት እንዲፈጠር እያደረጉ ያሉ ቦቲዎች ነዳጁን በፍጥነት ወደ ማደያ በማድረስ እንዲያሳውቁ የተላለፈውን ውሳኔ ያላከበሩ ኩባንያዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ በዚህም ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ውሳኔውን ያላከበሩ 10 የነዳጅ ቦቲዎች መወረሳቸውን ተናግረዋል።

በመንግሥት ቁጥጥር ስር የገቡ ነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ባለቤት የሆኑ ኩባንያዎች መለየታቸውን ጠቅሰው “ኅብረተሰቡ የሚጠቀምበትን ንብረት ወይም እቃ መከዘን” በሚል የወንጀል ህግ እንዲጠየቁ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በማደያዎች በኩልም ነዳጅ እያለ የለም የማለት፣ የማሸሽ፣ የመያዝና ሌሎች ችግሮች ላይ ቁጥጥር በማድረግ እርምጃ እየተወሰደ ሲሆን ከጅቡቲ በአማካኝ በየቀኑ 300 የነዳጅ ቦቴ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ በጅቡቲ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በቅንጅት ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ነዳጅን በ73 ብር ከውጭ ገዝታ 40 ብር ድጎማ በማድረግ ከ35 እስከ 36 ብር እየሸጠች ትገኛለች።

በዚህም መንግሥት በአንድ ዓመት 132 ቢሊዮን ብር ለድጎማ ወጪ ያደረገ ሲሆን ድጎማ በዝቅትኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኘውን ኅብረተሰብ ታሳቢ ያደረገ ቢሆንም በከፍተኛ የምጣኔ ሃብት ደረጃ ያሉትንም ተጠቃሚ ሲያደርግ ቆይቷል ነው ያሉት።

ከሐምሌ ወር 2014 ጀምሮ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኘውን ኅብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ሥርዓትን ለመተግበር በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር እየተዘረጋ ነው።

የቴክኖሎጂ አሰራሩን እውን ለማድረግም የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅትና ኢትዮ ቴሌኮም ትናንት ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል።

በነዳጅ ላይ የዋጋ ማስተካከያ ተግባራዊ ሲደረግ ከማስተካከያው በፊት የተጓጓዘው ነዳጅ ቀድሞ በነበረው ዋጋ እንዲሸጥ አስገዳጅ ሁኔታ መቀመጡን መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW