በጎንደር ግጭት የተሳተፉ ግለሰቦችን አድኖ ወደ ህግ እያቀረበ እንደሚገኝ መንግሥት ገለጸ

ሚያዝያ 21/2014 (ዋልታ) በጎንደር ከተማ በተፈጠረው ግጭት የተሳተፉ ግለሰቦችን አድኖ ወደ ህግ ለማቅረብ እየተሰራ እንደሆነና እስካሁንም በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ ድርጊቱን ከማውገዝ ባሻገር የሃይማኖት ግጭት እንዲቀሰቀስ እየሰሩ ያሉ ኃይሎች እንዲያቆሙ አሳስበዋል፡፡

ፍትሕን በመጠየቅ ሰበብ ሕዝበ ሙስሊሙን በማነሳሳት አብሮነትን በመሸርሸር፣ ሀገራዊ አንድነትን እና ኅልውናን ለማናጋት የሚደረገው ጥረት ተቀባይነት እንደሌለውም ገልጸዋል፡፡

ሁለቱም ሃይማኖቶች ከመከፋፈል ይልቅ ለዘመናት የዘለቀ ታሪካቸውን በማጠናከር አብሮነታቸውን ማጠናከር እንደሚገቡም አስገንዝበዋል፡፡

በአማራ ክልል ውስጥ አለመረጋጋት እንዲፈጠር እየሰሩ ያሉ ኃይሎች አሉ ያሉት ሚኒስትሩ ክልሉን የህገወጥ መሳሪያ እና ገንዘብ ዝውውር መናኻሪያ ለማድረግ እየሰሩ ያሉ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ የተከሰተው ድርጊት ሊወገዝ የሚገባው አጸያፊ ተግባር ነው ያሉት ሚኒስትሩ ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው እኩይ ተግባራቸውን ለመፈጸም የሞከሩ ግለሰቦችን በህግ ቁጥጥር ስር ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ወደ ወራቤ አካባቢ ግጭቱን ለማስፋፋት የተሞከረው የተናበበ እንቅስቃሴ የእስምናንም ሆነ የክርስትናን እንቅስቃሴ አይወክልም ያሉት ለገሰ (ዶ/ር) ይልቁንስ የኢትዮጵያ ጠላቶች በሀገር ውስጥ በሚገኙ ተላላኪዎቻቸው የከፈቱት አገር የማተራመስ ዘመቻ ነው ብለዋል፡፡

አንድን ወንጀል በሌላ ወንጀል ለመተካትና ችግሩን ለማወሳሰብ የሚንቀሳቀሱ የግጭት ነጋዴዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳሳበዋል፡፡

መንግሥት በጽንፈኞች ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥልና በአንዳንድ አካባቢ በመንቀሳቀስ ጥቃት እየፈጸመ በሚገኘው ሸኔ ላይ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝም አመላክተዋል፡፡