መንግሥት ባለፉት ስድስት ወራት 297 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን አስታወቀ

የካቲት 15/2014 (ዋልታ) በጦርነትና ሌሎች ውስብስብ ችግሮች ውስጥ በከረመችው ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የሚባል ገቢ ቢሰበሰብም መንግሥት ባለፉት ስድስት ወራት 297 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

የባለፉት 6 ወራት አገራዊ ወጪ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 39 በመቶ እድገት እንዳለውም አመላክተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሳወቁት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ ነው።

ያለፉት ስድስት ወራት የጦርነት ወቅት በመሆናቸው ምጣኔ ሃብቱ በዘርፈ ብዙ ፈተናዎች የታጠረ እንደነበርም አውስተዋል፡፡

በጠርነት ወቅት ብድር የሚሰጡ አገራት እና ተቋማት ብድር መስጠቱን፤ እርዳታ የሚያደርጉ ደግሞ እርዳታን ያዝ የማድረግ ሁኔታቸው ከፍ ያ ስለሚሆን ምጣኔ ሃብቱን በእጅጉ ይጎዱታል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም አምራቹ ኃይል በሙሉ ኃይሉ ከማምረት ይልቅ አንድም በአካል አሊያም በሐሳብ ወደ ጦርነቱ መግባቱ፣ የዜጎች መፈናቀል፣ መገደል፣ መደፈር እና መዘረፍ በስፋት መኖሩ ያለፉት ስድስት ወራት የምጣኔ ሃብቱ ተግዳሮቶች እንደነበሩም አስረድተዋል፡፡

ይህም ሆኖ ባለፉት 6 ወራት 185 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 171 ነጥብ 3 ቢሊዩኑን መሰብሰብ ወይም የእቅዱን 92 በመቶ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ይህ ገቢ ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር ሲታይ የ15 በመቶ እድገት እንዳለውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡

ይሁንና የመንግሥት ወጪ 297 ቢሊዮን ብር በላይ እንደነበረም ነው ያሳወቁት።

ኢትዮጵያ የምግብ ሸቀጦችን በከፍተኛ መጠን ማስገባቷ፣ የነዳጅና ማዳበሪያ ገቢ ምርቶች ከፍተኛ ወጪ መጠየቃቸው ለጭማሪው በምክንያትነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል፡፡

ባለፉት 2 ዓመታት የወጪ ምርት (ኤክፖርት) አቅምን 33 ከመቶ ማሳደግ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

በስድስት ወራቱ ደግሞ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ገቢ 25 በመቶ እድገት ያስመዘገበ ሲሆን ከ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት ተችሏል ብለዋል፡፡

ይሁንና ገቢ ምርቶቸን መተካት ላይ አመርቂ ውጤት ባለመገኘቱ ከውጭ ለሚገቡ ምርቶች የሚወጣው ገንዘብ መጠንም በተመሳሳይ የ25 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስረዱት።

በነስረዲን ኑሩ