መንግሥት ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ላላት ወዳጅነትና ጉርብትና ታላቅ ቦታ ትሰጣለች አለ

ኅዳር 20/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ያለውን የረጂም ጊዜ ወዳጅነት የሚፈታተን ትንኮሳ እየተደረገ ቢሆንም ኢትዮጵያ ወዳጅነቷን አስጠብቃ ትቀጥላለች ሲል መንግሥት ገለፀ፡፡
ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ላላት ጉርብትና ከፍተኛ ዋጋ የምትሰጥና ይህንንም በተግባር ማሳየት የቻለች አገር መሆኗንም አስረድቷል፡፡
ሱዳን የወረረችውን የኢትዮጵያ መሬት በተመለከተ የሁለቱን አገራት የቆየ ግንኙነት በማይጎዳ መልኩ እንደሚፈታ የኢትዮጵያ ፍላጎትና እምነት መሆኑንም አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በሱዳን በኩል ሰርገው የሚገቡ የጥፋት ኃይሎች በኢትዮጵያና ዜጎቿ ላይ ጥፋት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ መንግሥት እርምጃ እንደወሰደባቸው ጠቁመዋል፡፡
ይሁን እንጂ አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙኃን ይህንን ክስተት የሚዘግቡበት መንገድ የተሳሳተ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመው መንግሥት የሱዳን የመከላከያ ሰራዊት አባላትን አጥቅቷል የሚለው ዘገባ ሃሰተኛ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያና ሱዳን ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው አገራት እንደመሆናቸው ሱዳን በችግር ውስጥ በምትገባበት ወቅት ኢትዮጵያ ወዳጅነታቸውን እና ጉርብትናን በሚመጥን መልኩ ድጋፍ ማድረጓን መንግሥት ጠቁሟል፡፡
በሱዳን መንግሥት ክፍያ እየተፈጸመላቸው ባለፈው ሳምንት ሱዳን ውስጥ ሲመክሩ የነበሩ የሲኤንኤን፣ ሮይተርስ፣ ቢቢሲ፣ አልጀዚራና ሌሎችም ጋዜጠኞች የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሱዳንን ጦር እንደወጋ የሃሰት ዘገባን ሲያሰራጩ መሰንበታቸው ይታወሳል፡፡
በነስረዲን ኑሩ