መንግሥት ፋኖን ያደራጃል እንጂ ትጥቅ አያስፈታም ሲል የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ

ግዛቸው ሙሉነህ

ጥር 8/2014 (ዋልታ) መንግሥት ለአገር ኅልውናና ለሕዝብ ነጻነት የተጋደሉና ጀብድ የሰሩ ፋኖዎችን የበለጠ ያደራጃል እንጂ ትጥቅ አያስፈታም ሲሉ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ግዛቸው ሙሉነህ ገለፁ፡፡

በአማራ ሕዝብ ታሪክ ውስጥ የአማራን ሕዝብ ከጠላት የሚከላከል፣ ከውርደት የሚታደግና በልማትና በፖለቲካው መስክ ተጠቃሚ እንዲሆን ዋጋ የሚከፍል ሁሉ ፋኖ ነው ያሉ ኃላፊው፤ በመሆኑም መንግሥት ለአገር ኅልውናና ለሕዝብ ነፃነት የተጋደሉና ጀብድ የሰሩ ፋኖዎችን የበለጠ ያደራጃል እንጂ ትጥቅ አያስፈታም ብለዋል፡፡

‹‹የአሸባሪው ትሕነግ ቡድንን ወረራ ለመቀልበስ ፋኖዎች ትልቅ ጀብድ ፈጽመዋል፤ በማለትም መንግሥት ለእነዚህ ሰዎች እውቅና ሰጥቶ ይሸልማል እንጂ ትጥቅ የሚያስፈታበት ምክንያት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡

ፋኖ በክልሉ ላይ አደጋ በተቃጣ ጊዜ ከሌላው የመንግሥት የፀጥታ ኃይል ጋር ተቀናጅቶ ጠላትን እንደሚመክት አመልክተው፤ በሰላም ጊዜ ደግሞ ሁሉም ወደመደበኛ ሥራው ተመልሶ ሥራውን የሚከውን ኃይል ነው ብለዋል፡፡ ሥራ የሌለውን መንግሥት ወደሥራ እንዲገባ የሚያደርግበት ሁኔታ እንደሚኖርም ነው ያስረዱት፡፡

ፋኖ ሥርዓት የሚያከብርና ለአማራ ሕዝብ ጥቅም ራሱን መስዋዕት የሚያደርግ ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ ኢፕድን የጠቀሰው አሚኮ ሥርዓት አልበኛ የሆነ፣ ለመዝረፍ ለመስረቅና ሌላ ብጥብጥ ለማንሳት የሚንቀሳቀስ ኃይል ካለ ፋኖን የሚወክል ስላልሆነ የክልሉ መንግሥት በሕጉ መሰረት ሥርዓት እንደሚያስከብር መግለጻቸውን ጽፏል፡፡ ከዚህ ያፈነገጠና ሌላ ፍላጎት ያለው አካል ካለ ግን በፋኖ ስም መጠራት የለበትምም ብለዋል፡፡