መንግስት በህጻናትና በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል በትኩረት አየሰራ መሆኑ ተገለጸ

ኅዳር 15/2015 (ዋልታ) መንግስት በህጻናትና በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል በትኩረት አየሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ሴቶች እና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ገለጸ፡፡

“ሰላምና ምቹ የሆነች ኢትዮጵያ ለሁሉም ህፃናት” በሚል መሪ ሃሳብ የዓለም የህጻናት ቀን በሞጆ ከተማ እየተከበረ ይገኛል።

ቀኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ33ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍና በክልል ደረጃ ለ17ኛ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ አዘጋጅነት እየተከበረ ነው የሚገኘው።

በመደረኩ ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ሴቶች እና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ጀሚላ ሲምብሩ በቀድሞው ሥርዓት የህጻናትና ሴቶች መብት ያልተጠበቀ እና የተለያዩ ጥቃቶችን ሲያስተናግዱ መቆየታቸውን አስታውሰው አሁን ላይ ግን መንግስት በህጻናትና በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል በትኩረት አየሰራ መሆኑን ገልጸዋል::

ልጆች የሌላት ሀገር የወደፊት እጣ ሊኖራት ስለማይችል የህጻናት ጥቃትን ለመከላከል ሁላችንም ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን ብለዋል።

በመርኃ ግብሩ የተለያዩ ክንውኖች የሚካሄዱ ሲሆን የፓናል ውይይት፣ በሞጆ ከተማ አስተዳደር ለዓቅመ ደካማ የተገነቡ ቤቶች ርክክብ በማድረግ፣ ለዓቅመ ደካሞች የምግብ እና የቁስ ድጋፍ በማድረግ፣ የትምህርት ቤት ምገባ ማስጀመርያ ሥነ ሥርዓት በማካሄድ እንደሚከበርም ተጠቁሟል::

በመርኃ ግብሩ ላይ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ስንቄዎች፣ ህፃናት እና እናቶች፣ የሞጆ ከተማ ከንቲባ ካዲጃ ጀማል፣ የኦሮሚያ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ጀሚላ ሲምብሩ እና የዘርፉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

አስቴር ጌታሁን (ከሞጆ)

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW