መከላከያ ሠራዊት አሁን ለተፈጠረው አንፃራዊ ሠላም የበኩሉን ሚና ተወጥቷል – ሌተናል ጀኔራል ሀጫሉ ሸለመ

መከላከያ ሠራዊት

ታኅሣሥ 27/2015 (ዋልታ) መከላከያ ሠራዊት የገጠመውን ከፍተኛ የህልውና አደጋ በመቀልበስ አሁን ለተፈጠረው አንፃራዊ ሠላም የበኩሉን ሚና ተወጥቷል ሲሉ የመከላከያ ህብረት የሠው ሃብት አመራር ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ሀጫሉ ሸለመ ገለጹ።

የአዋሽ ቢሾላ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በዛሬው ዕለት በመሰረታዊ ውትድርና ያሰለጠናቸውን ምልምል ወታደሮች አስመርቋል።

በምርቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ሌተናል ጄኔራል ሀጫሉ ሸለመ እንደተናገሩት ሀገራችን ኢትዮጵያ ለሠላም ትልቅ ዋጋ የምትሠጥ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ለሠላም መስዋዕትነት የከፈለች ሠላም ወዳድ ሀገር ናት።

የጦርነትን አስከፊነት እና የሠላም ዋጋ ትልቅነትን ከምንም በላይ የምትረዳው ሀገራችን ኢትዮጵያ የጀመረችው የልማት ዕድገት እውን እንዲሆን ቅድሚያ ለሠላም ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መሆኗንም ገልፀዋል።

የልማት ዕድገታችን እና ሠላማችን እንዲረጋገጥ የአንበሳውን ድርሻ መከላከያ ይወስዳል ያሉት ጀኔራል መኮንኑ የገጠሙንን ከፍተኛ የህልውና አደጋ በመቀልበስ መከላከያ ሠራዊቱ የበኩሉን ተወጥቷል ብለዋል።

በየጊዜው አጀንዳዎቻቸውን እያቀያየሩ እኛን ለመፈተን ከመሞከር ወደ ኋላ የማይሉ ጠላቶቻችንን ለመከላከል ኢትዮጵያን የሚመጥን የመከላከያ ሀይል የመገንባት ተልዕኳችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።