መካነሰላም እና ከላላ ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል አገኙ

ታኅሣሥ 3/2014 (ዋልታ) መካነሰላም እና ከላላ ከተሞች ተቋርጦባቸው የነበረውን የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘታቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
በአሸባሪው ሕወሓት ቡድን የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት የወደመባቸው ከተሞች የኤሌክትሪክ አስተላላፊ መስመሮችንና ምሰሶዎችን በመጠገን የኤሌክትሪክ ኃይል መልሶ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት በደሴ ዲስትሪክት ስር የሚገኙትን ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ከሚሴ፣ ባቲ፣ ማጀቴ፣ ጨፋ ሮቢት፣ አቀስታ፣ መሀል ሳይንት፣ ሳይንት አጅባር፣ መኮይና አልብኮ ከተሞችን እስከ ታኅሣሥ 2 ኤሌክትሪክ የሰጠ ሲሆን አሁንም ሌሎች ቀሪ ከተሞችን ለማገኛኘት ጥረቱን አጠናክሮ ቀጥሏል ነው የተባለው፡፡
በዚህም የከተሞቻችንን ኤሌክትሪክ መልሰን ሳናገናኝ እረፍት የሚባል ነገር የለም በማለት ቆርጠው የተነሱት የደሴ ዲስትሪክት ሰራተኞች ዛሬ የመካነ ሰላም እና ከላላ ከተሞችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረጋቸውን ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡