ሚኒስቴሩ ህጻናትን ለማሳደግ ተረከበ

መስከረም 27/2014 (ዋልታ) የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር 15 ህጻናትን ተረክቦ ለማሳደግ ህጻናቱን ተረክቧል፡፡

ቀደም ሲል ሚኒስቴሩ ቃል በገባው መሰረት ህጻናቱን የተረከበው ከሜሪጆይ ህጻናት ማሳደጊያ ማዕከል መሆኑ ታውቋል፡፡

15ቱን ህጻናት ሚኒስቴሩና 4 ተጠሪ ተቋማት በጋራ እንደሚያሳድጓቸው በሚኒስቴሩ የአስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ምህረት ምናስብ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታ መስፍን አሰፋ (ዶ/ር) በበኩለቸው፣ ህጻናቱን ለማሳደግ ስንረከብ የሚሰማን የመንፈስ እርካታ ወደር የማይገኝለት ነው ያሉ ሲሆን ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ ከአብራካችን እንደወጡት ልጆቻችን ተንከባክበን ለማሳደግ ቃል እንገባለን ብለዋል፡፡

ህጻናቱ በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት በማምጣት ሀገር ተረካቢ ዜጋ እንዲሆኑ አስፈላጊው ድጋፍ እንክብካቤ እንደሚደረግላቸውም ገልጸዋል፡፡

የሜሪጆይ ህጻናት ማሳደጊያ ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማቱ ላደረጉት ድጋፍና እገዛ ምስጋና አቅርበው የመረዳዳት ባህላችን ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡