ሚኒስቴሩ ለኦሮሚያ ክልል 1.5 ቢሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

ጥቅምት 9/2015 (ዋልታ) የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ለኦሮሚያ ክልል 1.5 ቢሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉ የተደረገው በኦሮሚያ ክልል የሰላም እጦት ባለባቸው አካባቢዎች ለወደሙ መሰረተ ልማቶችና ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች ስትፈተን መቆየቷን የገለጹት ሚኒስትሯ በተለይም በአሸባሪው የትህነግ ቡድን በአፋርና አማራ ክልል የበርካታ ዜጎች ህይወት መቀጠፉን አንስተዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ በአፋር እና አማራ ክልሎች ካወደማቸው መሰረተ ልማትቶች ውስጥ 18 ተቋማትን መልሶ መገንባት ተችሏል ብለዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ለኦሮሚያ ክልል ያደረገው ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና የሚሻው እና ድጋፉ በሀገሪቱ የሚከሰቱ ችግሮችን ተደጋግፎ ማለፍ እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተናግረዋል፡፡

የተደረገው ድጋፍ ለሚፈለገው ዓላማ እንደሚውል እና ለተጎጂ ማህበረሰቦች ተደራሽ እንደሚሆን ርዕሰ መስተዳድሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

ክልሉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ምርትና ምርታማነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡፡

በአመለወርቅ መኳንንት

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW