የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በገጸ ድር አገልግሎት መስጠት ጀመረ

ነሃሴ 13/2013 (ዋልታ) – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚሰጣቸውን  ገልግሎቶች በገጸ ድር በመታገዝ መስጠት መጀመሩን ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ እና ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚሰጣቸውን የቪዛ አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችንም በኦንላይን መስጠት መጀመሩን ሚኒስትር ዲኤታዋ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ዛሬ ይፋ አድርገዋል፡፡

ይህ ይፋ የተደረገው የገጸ ድር አገልግሎት መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የውጭ ሀገራት ኤምባሲዎች፣ ዓለም አቀፍ እና አካባቢያዊ ድርጅቶች እንዲሁም በድርጅቶቹ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ቀልጣፋ እና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ሲሉ ሚኒስትር ዲኤታዋ ተናግረዋል፡፡

እንደ ሚኒስትር ዲኤታዋ ገለጻ ይህ አዲስ የገጸ ድር አገልግሎት መጀመር ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በቅልጥፍና እና በጥራት ለመስጠት የሚያደርገው ጥረት አንድ አካል ነው ብለዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የገጸ ድር አገልግሎት መስጫ ቴክኖሎጂው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ትብብር የበለጸገ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡