ሚኒስቴሩ በ2015 ከወጪ ንግድ ከ5.4 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ማቀዱን ገለጸ

ነሐሴ 10/2014 (ዋልታ) የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በ2015 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ከ5 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ማቀዱን አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የ2014 የጥራጥሬና ቅባት እህል የወጪ ንግድ አፈጻጸም እና የ2015 እቅድ ላይ ከላኪዎች ጋር እየተወያየ ነው።

በውይይቱ የተገኙት የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ትስስርና ወጪ ንግድ ፕሮሞሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ  ካሳሁን ጎፌ ሚኒስቴሩ በ2015 ከወጪ ንግድ 5 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ  ለማስገኘት ማቀዱን ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው በእቅዱ ከጥራጥሬና ቅባት እህል የወጪ ንግድ ከ595 ሚሊየን ዶላር በላይ ለመሰብስብ መታቀዱን ገልጸው ለዚህም በዘርፉ የተሰማሩ 955 ላኪዎች አቅማቸውን ማጎልበት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በመድረኩ በዘርፉ የተሰማሩ ላኪዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በእቅዱ የተቀመጠውን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ለማሳካት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እየመከሩ ሲሆን የህገ ወጥ ንግድ ለዘርፋ አሁንም እንቅፋት እንደሆነ ተገልጿል።

በ2014 በጀት ዓመት ከጥራጥሬና ቅባት እህል የወጪ ንግድ 478 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱ ተጠቁሟል።

ትዝታ መንግሥቱ (ከቢሾፍቱ)