ሚኒስቴሩ ባለፉት 6 ወራት ከ225 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ

ጥር 17/2015 (ዋልታ) የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፉት ስድስት ወራት 225 ነጥብ 93 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ያለፉት ስድስት ወራትን የስራ አፈጻጸም መገምገሙን የገለጹት የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ ለሀገሪቱ ልማት እና መልካም አስተዳደር ስራዎች ማስፈጸሚያ የሚውል በጀት ለመሰብሰብ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን አንስተዋል፡፡

በዚህም በ2015 በጀት ዓመት 450 ነጥብ 29 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራትም ሚኒስቴሩ 228 ነጥብ 23 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 225 ነጥብ 93 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 99 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር የ54 ነጥብ 62 በሊየን ብር ብልጫ ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ለግብር ከፋዮች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ እና ፍትሃዊ እንዲሁም ተደራሽ አገልግሎት መስጠት መቻሉ ለስኬቱ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል፡፡

ከሌብነት ጋር ተያይዞም የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸውን ባለሙያዎች እና ግብር ከፋዮች ላይ በጥናት ላይ የተመሰረተ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።

የግብር ስወራና ማጭበርበር እንዲሁም የህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ በሚፈለገው ደረጃ አለመሆን ለሚኒስቴሩ ባለፉት ስድስት ወራት የተስተዋሉ ተግዳሮቶች መሆናቸውም ተገልጿል፡፡

ያለንግድ ፈቃድ እየሰሩ ግብር የማይከፍሉ ዜጎችንም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ወደ ታክስ ሥርዓት እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በብሩክታይት አፈሩ