ሚኒስቴሩ ኢትዮጵያ ከባህልና ኪነጥበብ ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን አየሰራ መሆኑን ገለጸ

ግንቦት 25/2014 (ዋልታ) የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ከባህልና ኪነጥበብ ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን አየሰራ መሆኑን ገለጸ።
ክልል አቀፍ የባህል ፌስቲቫል እና ኤግዚቢሽን “ባህል ለዘላቂ ሠላምና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ሀሳብ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ አዘጋጅነት እየተካሄደ ባለው የባህል ፌስቲቫል እና ኤግዚቢሽኑ ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማሃዲ ኢትዮጵያ ከባህልና ኪነጥበብ ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን በትኩረት አየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ኤግዚቢሽንና ፌስቲቫሉ በክልሉ የሚገኙ መልካም እሴቶችን ለማስተዋወቅ የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸው ሚኒስቴሩ የክልሉን ዕደ ጥበብ፣ ሥነ ጥበብና ባሕላዊ ዕሴቶችን ለመደገፍና አብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋገሾ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት ታሪካዊ እና ባህላዊ እሴቶች በሕዝቦች ዘንድ የፈጠሩ መልካም መስተጋብሮችን አጠናክሮ ለማስቀጠል መድረኩ የጎላ ሚና እንዳለው አመላክተዋል።
ክልሉ የተለያዩ ባህላዊ እና ማኅበራዊ እሴቶች ያሉበትና ለሀገሪቱ አንድነት አስተዋጽኦ እያበረከቱ የቆዩ መሆናቸውን ያስታወሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንን ለማበላሸት የሚሰሩ እኩይ ዓላማ ያላቸው አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
በክልሉ ያሉ ቋንቋችን እና ባህሎችን ለማሳደግ ሁሉም የአካባቢው ማኅበረሰብ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ፋንታሁን ብላቴ በበኩላቸው የባህል ኤግዚቢሽንና ፌስቲቫሉ በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚካሄድና ባህሉን፣ ቋንቋውን፣ ታሪኩንና አብሮነትን የሚያጎለብት መሆኑን ተናግረዋል።
በኤግዚቢሽንና ፌስቲቫሉ ላይ የተለያዩ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣ የ6ቱ ዞኖች ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣ የባህል አምባሳደሮችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
የባህል ፌስቲቫል እና ኤግዚቢሽኑ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ግንቦት 27/2014 ዓ.ም ለሦስት ተከታታይ ቀናት በተለያዩ መርኃ ግብሮች ይከበራል፡፡
አድማሱ አራጋው (ከቦንጋ)